አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ጋር ምክክር አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ጋር ምክክር አደረጉ
ሐምሌ 10 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳኡዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ተሚሚ አል-ደውሰሪ ጋር በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎችን በሚመለከት ምክክር አደረጉ፡፡
አምባሳደሩ አርባ ሁለት ሺህ (42 000) ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ዘመቻ ሥራ መጠናቀቅን፣ በማቆያ ማእከላትና በእስር ቤቶች ያሉ ዜጎችን በቀጣይ ወደ አገር መሸኘት በሚቻልበት መንገድ፣ በማቆያ ማእከላትና በእስር ቤቶች ያሉ ዜጎችን አያይዝ፣ እንዲሁም የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ህገ ወጥ ዜጎችን በሚመለከት የሚያካሂደውን የእስር ዘመቻ በተመለከተ ምክክር አድርገዋል።
በተጨማሪም ወደ አገር መመለስ ፈልገው በተለያዩ ምክኒያቶች ወደ አገር መመለስ ያልቻሉ በራሳቸው የትኬት ወጭ ያለምንም እስርና ገንዘብ መቀጮ የሳኡዲ አረቢያ ምህረትን ተጠቅመው ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል።
ምህረት ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥያቄው ለሳኡዲ አረቢያ ንጉስ ሠልማን ቢን አብዱልአዚዝ ቀርቦ ለኢትዮጵያውያን ምህረት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይነት ኤምባሲው የምዝገባ መርሀ ግብር በመክፈት የጉዞ ሂደቱን እንደሚጀምር መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።