በሐረሪ ክልል ለተተከሉ ችግኞች ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ከግብ ማድረስ ይገባል---አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለተተከሉ ችግኞች ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ከግብ ማድረስ ይገባል---አቶ ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ ሐምሌ 10/ 2013 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ለተተከሉ ችግኞች ህብረተሰቡ ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ከግብ ሊያደርስ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
በአንድ ጀምበር ከ350 ሺህ በላይ ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ዛሬ በክልሉ ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በየደረጃው ኮሚቴዎች ተቋቁመው ችግኞችን የማፍላት እና መትከያ ጉድጓዶችን የማዘጋጀት ሥራ ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አውስተዋል።
በተጨማሪም የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ሥራዎች ሲሰሩ እንደነበርም እንዲሁ።
"በአሁኑ ወቅትም ህብረተሰቡ ችግኝ የመትከል አስፈላጊነትን ተገንዝቦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን በተነሳሽነት ጥረት እያደረገ ይገኛል" ብለዋል፡፡
ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት በክልሉ በገጠርና በከተማ የሚገኘው ነዋሪ በራሱ ተነሳሽነት በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም አቶ ኦርዲን ጠቆመዋል።
በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ አካላት፣ የሴክተር መስሪያ ቤት ሠራተኞች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት የነቃ ተሳትፎም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ህብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁና ለታለመላቸው ግብ እንዲደርሱ ተገቢ እንክብካቤ በማድረግ ከግብ ሊያደርስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ 3 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደስራ መገባቱን ገልጸዋል።
ከሚተከሉት 60 በመቶው ጥምር ደን ሲሆኑ 40 በመቶው ደግሞ የደን ዛፎች ናቸው ብለዋል፡፡
ዛሬ በተካሄደው አንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር በሁሉም ቀበሌዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ350 ሺህ በላይ ችግኞች ተከላ መካሄዱን አስታውቀዋል፡፡
ይህም ባለፈው ዓመት በአንድ ጀምበር ከተተከሉ ችግኞች ቁጥር እጥፍ መሆኑንም አመላክተዋል።
የሚተከሉ ችግኞች ለምግብነት፣ ለመድሃኒትነት እንዲሁም ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የጎላ ፋይዳ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉ መካከል የሶፊ ወረዳ ነዋሪው አቶ መሀመድ አብዱሰላም ችግኝ ከመትከል ባለፈ በዘላቂነት እንዲፀድቅ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የችግኝ ተከላ ሥራዎች በአካባቢው አዎንታዊ ለውጥ መታየት መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡
ወጣት ከዲር ዩሱፍ በበኩሉ፤ ከችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አወስቷል፡፡
በክልሉ በተካሄደው አንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻር መርሃ ግብር ችግኝ በመትከል መሳተፉንና በቀጣይም ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን እንደሚንከባከብ አስታውቋል።
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከስፍራው ዘግቧል፡፡