ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የፖሊስ አቅም መገንባት ወሳኝ ነው...ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2013(ኢዜአ) በፖሊስና በህብረተሰቡ መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የፖሊስ አቅምን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን የፖሊስ መኮንኖች ዛሬ አስመርቋል።

ሰንዳፋ በሚገኘው ፖሊስ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው የምርቃት ሥነ-ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች ተገኝተዋል።     

ሠልጣኞቹም በፖሊስ ሳይንስ፣ በስነ-ወንጀልና ወንጀል ፍትህ፣ በነርሲንግ፣ ፖሊስ ማኔጅመንት እንዲሁም በፖሊስ መኮንንነት ዘርፍ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ዩንቨርስቲው ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎችን አስመርቋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ወንጀልን መከላከልና ህግን ማስከበር አንድ ማህበረሰብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመራ መሰረት የሚጥል ነው።   

ይህን ለማድረግ ዛሬ "የተመረቃችሁ የፖሊስ መኮንኖች ክህሎትና ሥነ ምግባር እንደጨበጣችሁ እምነቴ ነው" ሲሉም አክለዋል።   

"አገራዊ ለውጡ ግቡን እንዲመታ ጠንካራ ተቋማት አስፈላጊ ናቸው" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ተማራቂዎች ያለልዩነት ህዝቡን ማገልገል እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል።  

በአንጻሩ ህዝቡ "ፖሊስ የሚሰራውና የቆመው ለኔ ነው" የሚል አስተሳሰብ ሊያዳብር እንደሚገባ አጽንኦት የሰጡት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት።  

ወቅቱ ከምንም ጊዜ በላይ ሠላምን አጥብቀን የምንሻበት ጊዜ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፤ ችግሮች ሲያጋጥሙ ሠላማዊ መፍትሄ መሻት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።   

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ የፖሊስ መኮንኖች ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ጫና ተገንዝበው ለበለጠ ሃላፊነት ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ለዚህም ተመራቂ መኮንኖች የቀሰሙትን ክህሎት ከተግባር ጋር በማዋሃድ ሃላፊነታቸውን እንዲሚወጡም አስገንዝበዋል።

የዩንቨርስቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አበበ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርስቲው ከኢትዮጵያ አልፎ በቀጣናው የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው።

ለዚህም የሚሰጠውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል የስርዓት ትምህርት ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈ ጥናትና ምርምር ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ከደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ ለተውጣጡ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

ተመራቂ ዕጩ መኮንኖች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በአግባቡ በመተግበር አገርና ህዝብ የጣለባቸውን ሃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በየትምህርት ዘርፉ  የላቀ ውጤት ላመጡ ተመራቂ መኮንኖች ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

በዩኒቨርስቲው ለረጅም ዓመት ያስተማሩ ሁለት አንጋፋ መኮንኖች የህይወት ዘመን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለ38 ዓመታት ያስተማሩት ምክትል ኢንስፔክተር እያሱ ለቴቦ እንዲሁም ለ37 ዓመታት በዩንቨርስቲው ያገለገሉ ምክትል ኮማንደር ባህሩ መንገሻ የዋንጫና ገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።  

ዩንቨርስቲው ከተቋቋመ 74 ዓመታትን ያስቆጠረ  ሲሆን፤ በቅርቡም ከኮሌጅ ወደ ዩንቨርስቲ ማደጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም