የገጠሙንን ችግሮች እየፈታን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ስራዎችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- ልማት ባንክ - ኢዜአ አማርኛ
የገጠሙንን ችግሮች እየፈታን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ስራዎችንን አጠናክረን እንቀጥላለን- ልማት ባንክ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) "የገጠሙንን ችግሮች እየፈታን ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ስራዎችንን አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ተናገሩ።
የባንኩ ዋና መስራቤት ሰራተኞች በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል ከጉለሌና ከቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ጋር በጋራ በመሆን 3 ሺህ 675 አገር በቀል ችግኞችን ዛሬ ተክለዋለው።
ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ዮሐንስ አያሌው፤ ባንኩ በአገሪቱ ልማት ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ሲሆን ከዚህም ጎን ለጎን የችግኝ ተከላ አንዱ አካል አድርገን እንሰራለን ብለዋል።
ችግኝ ከመትከል በተጨማሪ የመንከባከብ ስራ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 18 ሺህ ችግኞችን የባንኩ ሰራተኞች መተከላቸውንም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
ባንኩ በጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል አካባቢ ቦታ በመረከብ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ''ውብ አረንጓዴ መናፈሻ ፓርክ'' በራሱ ማልማቱን ጠቁመዋል።
ለችግኝ ግዥና ለሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ለሁለቱም ክፍለ ከተሞች ባንኩ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ባንኩ በየዓመቱ ለአረንጓዴ አሻራ ድጋፍ በማድረግ ኢትዮጵያን የማልበስ ጉዞውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማው የዋና ስራ አስፈጻሚ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ሲሳይ እንዳለ በክፍለ ከተማው እስከአሁን ከ800 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የነዋሪው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያመላክት ጠቁመው ነዋሪዎች በራስ ተነሳሽነት ችግኞችን በመትከልና እንክብካቤ ማድረጋቸው አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተገኙት ሰራተኞችም ችግኞችን ከመትከል በተጨማሪ ለመንከባከብም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተያዘው ክረምት 6 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።