ከመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተጓዳኝ ለአረንጓዴ ልማት ስኬትም እንደሚሰራ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ገለጸ

ሀምሌ 10/2013 የመንገድ ተደራሽነትን ከማስፋት በተጓዳኝ ለአረንጓዴ ልማት ስኬትም የድርሻውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ መንግዶች ባለሰልጣን ሰራተኞች በሀዋሳ ሞጆ መቂ የፍጥነት መንገድ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂር መሐመድ አብድረሂም፤ ባለስልጣኑ የመንገድ ተደራሽነትን ከማስፋት በተጓዳኝ ለአረንጓዴ ልማት ስኬትም የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

በመንገድ ፕሮጀክቶች አካባቢ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶች በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ችግኞችን በመትከል አካባቢው አረንጓደ እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት።

"ዛፎች ለመንገዶችም ውበት ናቸው" ያሉት ኢንጂር መሐመድ መንገዶች እየተገነቡ አካባቢዎችም ውብና አረንጓደ እንዲሆኑ አንሰራለን ብለዋል።

በሚገነቡ መንገዶች የሚቆረጡ ዛፎችን በእጥፍ የመተካት አላማ ሰንቆ ባለስልጣኑ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዛሬው እለት በሀዋሳ ሞጆ መቂ የፍጥነት መንገድ የተተከሉት ችግኞችም የዚሁ እንቅስቃሴ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በመንገዶች ባላስልጣን የኤክስፕረስ መንገዶች ዳሬክተር አቶ ናሆም ጸደቀ፤ በ“ኢትዮጵያን እናልብስ” መርሃ ግብር ባለስልጣኑ ጉልህ አስተፅኦ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የደን ሽፋን እንዲሻሻልና የአካባቢና የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት በቀጣይም በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በዘንድሮው የአራንጓዴ  አሻራ መርሃ ግብር 2 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም