ቀጥታ፡

የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን-- በድሬዳዋ ዑጋዞችና አባገዳዎች

ድሬዳዋ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር የሚደረገው ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ በድሬዳዋ ዑጋዞች፣ አባገዳዎችና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች ገለጹ።

ህግ ለማስከበር በሚካሄደው ዘመቻ ለመሳተፍ ለተዘጋጁ የድሬዳዋ ልዩ ኃይል አሸኛኛት በተደረገበት ስነ-ሰርዓት ላይ ከተገኙት መካከል የኢሣ ማህበረሰብ ኡጋዝ ተወካይ አቶ መሐመድ ሙሴ የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ለሚከናወኑ  ተግባራት  አስፈላጊውን  ድጋፍ እንደሚያደረጉ ገልጸዋል።

የህወሓት አሸባሪ ቡድን ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገርን ለማፍረስና የሕዳሴው ግድብ እንዲደናቀፍ የሚያደርገው ጥረት በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንደሚከሽፍ  ተናግረዋል።

"ጁንታው ህወሓት ራሱ ይፈርሳል እንጂ ሀገር በልጆቿ ተከብራ ትሻገራለች" ያሉት ደግሞ የአፈንቀሎ አባገዳ አብዱማሊክ አህመድ ናቸው፡፡

ለሠራዊቱ በገንዘብ፣ በቁስና እውቀት ድጋፍ ማድረግን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የጉርጉራ ማህበረሰብ ዑጋዝ ዚያድ ዳዊድ በበኩላቸው፤ የሀገርን ህልውና  ለማስከበርና  አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው  የአንድነት  ጉዞ  መጠናከር  እንዳለበት ተናግረዋል።

በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው ህብረተሰብ አንድነቱን ጠብቆ የአካባቢውን ሰላምና ልማት ከመጠበቅ ባለፈ ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አድርገዋል፡፡

"የሕዳሴው ግድብ እንዲጠናቀቅ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን"  ሲሉም አክለዋል።

በአስተዳደሩ የሀገር ሽማግሌ  አቶ አልይ ዩሱፍ እንዳሉት፣ ህወሓት መንግስት ለክልሉ ህዝብ በማሰብ የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ሳይቀበል የጥሞና ጊዜውን ለሌላ ጥፋት መጠቀሙ የሚያሳዝን እኩይ ተግባር ነው፡፡

"ሽብርተኛውን ህወሓት ለህግ ለማቅረብና የሀገርን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም የዜግነት ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡

ሌላው ነዋሪ አቶ ኤሊያስ ደለለኝ፤ ሠራዊቱ ከየክልሉ ከተውጣጡ ልዩ ኃይሎች ጋር ተቀናጅቶ ሀገር ለማፍረስ እየተጋ ያለውን ሽብርተኛ ቡድን ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል።

ለሀገር ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ጠንቅ የሆነውን ትህነግ የሚደግፉ አካላትና ተቋማትን በመጠቆም የሀገርን ህልውናን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡም  ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ጭፍጨፋ ሁሉም ተረባርቦ ማስቆም እንዳለበት ያመለከተው ደግሞ ወጣት ከድር አሊይ ነው፡፡

"ዜጎች ባላቸው አቅም ሁሉ ከሠራዊቱ ጎን በመቆምና በመደገፍ የሀገር አለኝታነታችንን የምናሳይበት  ጊዜ መሆኑን መገንዘብ  ይገባል" ብሏል።

ኃያላን መንግስታት እና መገናኛ ብዙሀን በህጻናት ላይ እየተፈፀመ ያለውን ዓለም አቀፍ ወንጀል እንዲያወግዙ ዲፕሎማቶችና ኢትዮጵያዊያን ጫና ሊፈጥሩ እንደሚገባም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም