ተመራቂ ተማሪዎች በህዳሴው ገድብ የተገኘውን የዴፕሎማሲ ድል እንዲጠናከር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች በህዳሴው ገድብ የተገኘውን የዴፕሎማሲ ድል እንዲጠናከር የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ
አሶሳ ፤ሐምሌ 10 / 2013 (ኢዜአ) የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች በህዳሴው ግድብ የተገኘውን የዲፕሎማሲ ድል እንዲጠናከር እውነታውን ለዓለም በማስገንዘብ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ፡፡
ዩኒቨርሲቲው 2 ሺህ 277 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጠናከረ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው፡፡
የግድቡን ስራ እና ስድስተኛውን ምርጫ ለማደናቀፍ የውስጥ እና የውጪ ሃይሎች ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት አንድ ሆነው በመረባረብ መቀልበስ ችለዋል ብለዋል፡፡
የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችም በህዳሴው ገድብ የተገኘውን የዲፕሎማሲ ድል እንዲጠናከር እውነታውን በማህበራዊ ትስስር ገፆች ለዓለም ማህበረሰብ በማስገንዘብ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲውን በ2022 ዓ.ም ከሃገራችን አምስት ተቀዳሚ የልህቀት ማዕከላት አንዱ ለማድግ ራዕይ አስቀምጦ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
ምህንድስና፣ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ከርሰምድር ጥናት እና ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ትኩረቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እቅዱን ለማሳካት የጥናት እና ምርምር ስራዎችን ከማጠናከር ጀምሮ የማስፋፊያ ግንባታዎች እና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር ከማል እንዳስታወቁት፤ ዛሬ ለስምንተኛ ጊዜ ከተመረቁት 2 ሺህ 277 ተማሪዎች መካከል 65 በሁለተኛ ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን ከእነዚህም 37 በመቶው ሴቶች ናቸው፡፡
በ2004 ዓ.ም. ስራ የጀመረው አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ 15 ሺህ ያህል ተማሪዎችን ማስመረቁ ተመልክቷል፡፡