የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ተመራቂ ተማሪዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ተመራቂ ተማሪዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና በመቀልበስ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ተመራቂ ተማሪዎች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያስተማራቸውን ከ2ሺ33 በላይ የቅድመ መደበኛና የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በትብብር በድህረ ምረቃ ዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን 153 እጩ ዲፕሎማቶችንም እንዲሁ በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚንስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር አቶ በዛብህ ገብረየስን ጨምሮ ሌሎች ኃላፊዎች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት፤ መንግስት ሲቪል ሰርቪሱን በአሰራርና በአደረጃጀት ለመለወጥ እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች ውስጥ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ ብቃት ያለው የመንግስት አገልግሎት መገንባት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተቀይሷል።
ፍኖተ ካርታው እውን እንዲሆን ዩኒቨርሲቲውን ጨምሮ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና ተጠሪ ተቋማቱ ሚና አይተኬ መሆኑንም ገልፀዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለይ የሰው ኃይል በመገንባት ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለመገንባትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ፣ አገሪቷ ያጋጠማትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና በመቀልበስ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የኅብረተሰቡን ርብርብ እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ለብሄራዊ ህልውናና ደህንነት እንዲሁም አገራዊ መግባባት ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተው፤ መምህራንና ተማሪዎች በዚህ ረገድ አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እንዳሉት፤በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ በመጠቀም ዩኒቨርሲቲው የሪፎርም ተግባራትን እያከናወነ ነው።
የተማሪዎች ምልመላ፣ መረጣና ቅበላ ፖሊሲና ፕሮቶኮል መቀየሩንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተያዘው ክረምት ጀምሮ የሲቪል ሰርቪሱን አቅም ለመገንባት የክረምት የወጣቶች አቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
የትምህርት መርሃግብሮቹን አገሪቷ ካላት ፍላጎትና የደረሰችበት እድገት መሰረት ያደረገ እንዲሆን ስርዓተ ትምህርቶችን በመከለስ አዳዲስ መርሃ ግብሮችን ለመክፈት የሚረዱ ስርዓተ ትምህርቶች መቅረፁንም አስረድተዋል።
የምርምርና ማማከር ዘርፉን ለማደራጀትና መሰል ሥራዎችን ለመከወን የምርምር አበልፅጎት ማዕከል መደራጀቱን በማብራራት፤ በዚህም ከተለያዩ ተቋማት ጋር 30 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ የማማከርና የምርምር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ማስረከቡን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው አቅሙን ለመገንባት የሰው ኃይሉን እያሰለጠነና የተለያዩ ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 27 ዓመታት ከ50ሺ በላይ ተማሪዎችን ከዲፕሎማ እስከ ፒ.ኤች.ዲ አስተምሮ አስመርቋል።
ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ አገር ተማሪዎችን ማስመረቁንም ተናግረዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ባገኙት እውቀት አገራቸውንና ህዝብን ለማገልገል እንደሚተጉ በመግለጽ፤ አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍና አንድነትን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ነው የጠቆሙት።