ተመራቂዎች የሰላምና መቻቻል እሴቶችን በማጎልበት የሀገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን ተግተው መስራት አለባቸው --ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች የሰላምና መቻቻል እሴቶችን በማጎልበት የሀገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን ተግተው መስራት አለባቸው --ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 10/1013 (ኢዜአ) ተመራቂዎች በሚሰማሩበት መስክ የሰላምና መቻቻል እሴቶችን በማጎልበት የህዝባቸውንና ሀገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን ተግተው መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ኤክስኪዩቲብ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተልዮሐንስ አሳሰቡ።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 356 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ እንዳሉት፤ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በምርምር፣ በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በቅርቡ በተደረገ በዩኒቨርሲቲዎች የትኩረት መስክና ተልዕኮ የመለየት ሥራ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቡ የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን መመረጡን ገልጸዋል።
በቀጣይም ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በብዛትና ጥራት በማፍራት ኢትዮጵያ የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት ይበልጥ ጠንክሮ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ተመራቂዎችም በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በሚሰማሩበት መስክ የሰላምና የመቻቻል እሴት በማጎልበት የህዝባቸውንና ሀገራቸውን ዕድገት ለማፋጠን ተግተው እንዲሰሩም አሳስበዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ምርምር ዘርፎች ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬም በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሰለጠኑ 2ሺህ 356 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ማስመረቃቸውን አስታውቀዋል።
ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥም 726 ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚመደብ ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅትም 372 የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት መርሃ ግብሮች እንዳሉት ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው በ "ወተር ሪሶርስ ኢንጅነሪንግ ኤንድ ማኔጅመንት " የትምህርት ዘርፍ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ዶክተር ሲሳይ አስረስ በሰጠው አስተያየት፤ በተማረበት መስክ ህዝቡንና ሀገሩን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጿል።
በህዝብ አስተዳደር በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቀችው እስከዳር አድማስ በበኩሏ ''በተማርኩት የትምህርት መስክ ሀገሬንና ህዝቤን ለማገልገል ተዘጋጅቻለሁ'' ብላለች።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ መገለጹን የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።