የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትግራይን የተመለከቱ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን እያሰራጩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትግራይን የተመለከቱ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን እያሰራጩ ነው

ሐምሌ 10 / 2013 (ኢዜአ) ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለመላው የዓለም ህዝብ ወኪል ሆነው የአለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት እያገለገሉ ቢሆንም ለአንድ በአሸባሪነት ለተፈረጀ የህወሓት ቡድን ሽፋን ለመስጠት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ይመስላል።
ድርጊታቸው እንደ አንድ የዓለም ዓቀፍ ድርጅት መሪ ሳይሆን ወገንተኛነት የተጫነው የአንድ ቡድን አክቲቪስት መምሰል ከጀመሩም ውሎ አድሯል።
በተባበሩት መንግስታት መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 37 ላይ "ዋና ዳይሬክተር እና ሰራተኞቹ ተግባራቸውን በሚፈፅሙበት ወቅት ከማንኛውም ከድርጅቱ ውጭ ከሆነ ባለስልጣንም ሆነ መንግስት መመሪያ መጠየቅ ወይም መቀበል የለባቸውም ” ይላል።
ይህ ሆኖ ሳለ ዋና ዳይሬክተሩ በተባበሩት መንግስታት ተቋማት በሃላፊነት የተቀመጠ ሰው በግል ጉዳዮች ላይ የራሱን አስተያየት እና ስሜት መግለጽ የሚከለክለውን ህግ ችላ ማለታቸውን ያመላክታል።
በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የህወሃት ቡድን የአገርን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ ከ20 አመት በላይ የትግራይ ህዝብን ሲጠብቅ በኖረው የአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በማድረስ ቀይ መስመር በማለፉ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደተወሰደበት ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎም የቡድኑ ስራ አስፈጻሚ አባል ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ የዓለም ዓቀፍ ተቋምን እየመሩ ቢገኙም ዛሬም የቡድኑን ጥፋት ለመሸፋፈንና ነፍስ ዘርቶ እንዲመጣ ለመደገፍ እየተፍጨረጨሩ ይገኛሉ።
ባለፈው አንድ ወር ብቻ የግለሰቡን ማህበራዊ ገጽ ብንመለከት ስለሌላው ዓለም ክፍል አንድም ነገር ሳይተነፍሱ አሸባሪውን ቡድን በመደገፍና የኢትዮጵያን መንግስት ለመወንጀል በሚመስል መልኩ የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
መልዕክት ብቻ ሳይሆን አሁን አሁን ፍላጎታቸው ግልጽ እየሆነ የመጡ መገናኛ ብዙሃንን የተሳሳቱ መልዕክቶች አጋርተው ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ሞክረዋል።
በተለይ መንግስት ወቅቱ የእርሻ በመሆኑ አርሶ አደሩ ይረስ፣ የትግራይ ህዝብም የጥሞና ጊዜ ይሰጠው በሚል የወገተኝነት ስሜት መቀሌን ለቆ በወጣበት ወቅት የህወሓት አሸባሪ ቡድን የደረሰበትን የስነ ልቦና ስብራት ማካካሻ እንዲሆነው አሸንፌ መቀሌን ተቆጣጠረ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡
የህወሓት አሸባሪ ቡድን መቀሌ መግባቱን ተከትሎም በተለያዩ የአለም ሀገራት የሚገኙ የቡድኑ ደጋፊዎች “አሸነፍን” እያሉ በተለያዩ ማህበራዊ ገጻቸው ህዝብን ለማደናገር ሞክረዋል።
ለአብነትም ከነዚህ አደናጋሪ መልዕክቶች መካከል "እውነት ያሽንፋል" "ኮራሁ" የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች የወቅቱ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው፡፡
ለአብነት በማይናማር፣ ከሰሞኑ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ስለሆነው ነገር ግድ ያልሰጣቸው ዶክተር ቴዎድሮስ አሁን ላሉበት ደረጃ ያደረሰቻቸውን ኢትዮጵያን ለመወንጀል እየተካሄደ ያለውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ መታየታቸው ግለሰቡ የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ተወካይ ሳይሆኑ፤ የአንድ አሸባሪ ቡድን አክትቪስት መሆናቸውን ያሳብቅባቸዋል።
አለም አቀፉ ገለልተኛ የፋይናንስ ተቋም (ኢንዲፔንደንት ፋይናንሽያል ኦዲት) ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በዋና ዳይሬክተርነት በሚመሩት የአለም ጤና ድርጅት ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ማጭበርበር፣ ጾታዊ ጥቃትና የሙያ ደረጃዎችን ያልጠበቁ አሰራሮች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ሳምንት የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ የ2020 አመታዊ አፈጻጸምን በተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት እንዳመለከተው፤ በተቋሙ እየጨመረ የመጣውን የሥነ ምግባር ጉድለት ማጭበርበርና ጾታዊ ጥቃት ተከትሎ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ጊዜ እንዳይመረጡ የአለም ኤች አይቪ ኤድስ ሄልዚኬር ፋውንዴሽን ጠይቋል።

በአለም ጤና ድርጅት ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት፤ማጭበርበርና ጾታዊ ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱም መጠየቁ ይታወሳል።
በሪፖርቱ መሰረት በ2020 የበጀት አመት የአለም ጤና ድርጅት ከ332 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከአሰራር ውጪ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ማድረጉም ተገልጾ ነበር።