ቀጥታ፡

ከውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና ለመላቀቅ ሀገራዊ ጥቅምን የማስከበር ዲፕሎማሲን ማጠናከር ያስፈልጋል-- የታሪክ ምሁራን

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያጋጠማት ካለው የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና ለመላቀቅ ሀገራዊ ጥቅምን የማስከበር ዲፕሎማሲ ስራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ጠንካራ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራ እንደሚያስፈልግ የታሪክ ምሁራን ገለጹ፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር  ታምራት መነሻ  እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ናት።

ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ ከሌሎች ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው በርካታ ግንኙነቶች በየዘመናቱ እየተቀያሩረ መጥተዋል።

ይህንን የካበተ ልምድ በመጠቀም አሁን ላይ በሀገር ላይ የተቃጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመቀልበስ  ሀገራዊ ጥቅምን ማስቀደም ላይ ያተኮረ የውጭ ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የውጭ ዲፕሎማሲውን ለማስፋት በርካታ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን የከፈተች  ሀገር እንደመሆኗ መጠን ይህንን በመጠቀም በተለይ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ  የገጠማትን አታካራ ልታስቆም እንደምትችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካን ህብረት ከመመስረት ጀምሮ ተሰሚነት ያላት ሀገር ናት ያሉት ሙህሩ፤ የአፍሪካዊያን ጉዳይ በአፍሪካዊያን እንዲፈታ ህብረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

በቅርቡ በጸጥታው ምክር ቤት የታየው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ውሃ ሙሌትም በአፍሪካ ህብረት እንዲወሰን መደረጉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።

የታሪክ ምሁሩ ፤ ሃገራት በተፈጥሮ ሀብታቸው በመጠቀም ምጣኔ ሀብታቸውን  እያሳደጉ ሲመጡ በርካታ ጫና ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ ላይ  እየደረሰ  ያለው ጫና ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ አመላክተዋል።

ማናቸውም ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ድርድርን መሰረት ያደረጉና ግንኙነቶችን የማያበላሹ እንዲሆኑ ለማድረግ የዲፕሎማሲ ስራ ወሳኝነት እንዳለው አውሰተዋል።

 በሃዋሳ መምህራን ኮሌጅ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተጠሪ  መምህር ስንታየሁ ደመቀ በበኩላቸው ፤ አሁን ላይሀገሪቱ በውስጥም በውጭም ጫና ውስጥ የወደቀችበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነቱን ችግር ከዚህ ቀደምም አልፈነዋል ያሉት መምህሩ፤ የኢጣሊያን ወራሪ ላይ የተገኘው ድል ሃገራዊ  አንድነትን  በማጠናከርና  በእውቀት  ላይ  በተመሰረተ   ዲፕሎማሲ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ አስመልክቶ የተካሄደው አለም  አቀፍ  መድረክም ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ የተከናወነበትና ውጤት የተገኘበት እንደሆነ አውስተዋል።

ሀገሪቱ አሁን ካጋጠማት የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶች ለመሻገር መደበኛ ከሆነው የዲፕሎማሲ ስራ ባሻገር በሀገር ውስጥና በተለያዩ አለም ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ታዋቂ  ሰዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራትን በቅንጅት መምራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በርካታ ታሪካዊ ክስተቶቻችን የሚያሳዩት በሃገራዊና ህዝባዊ አንድነት አሸናፊ መሆናችንን ነው፤ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ  አልምተን ከድህነት  መውጣት   ቀዳሚ  አጀንዳችን  ነው በማለት አስተያየታቸውን  ሰጥተዋል።

ለዚህ ስኬት ማሳያ የሆነው የህዳሴ ግድብ ከዳር እንዲደርስ  ህዝቡ የጀመረው ተሳትፎ ሊያጎለብት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የዲፕሎማሲ ስራውና የውጭ ግንኙነቱን በባለሙያና በእውቀት መምራት በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ አሸናፊነትን ያጎናጽፋል ያሉት መምህሩ  ለዚህም ዲፕሎማሲውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም