በህወሓት የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እናደርጋለን-- በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት - ኢዜአ አማርኛ
በህወሓት የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እናደርጋለን-- በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) በህወሓት የጥፋት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያ ኃይል ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል የአደረጃጀት ዘርፍ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ገለጹ።
የክልሉን ህብረተሰብ ለማነቃነቅ ሁሉን አቀፍ የሀብትና የፋይናንስ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን የኮሚቴው አባላት በንቅናቄ ዕቅዱ ላይ መክረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ፣ ክልላዊ የሀብትና ፋይናንስ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፋጤ ሶርሞሎ እንዳሉት፤ በጁንታው የተቃጣው ትንኮሳ ለተወሰነ ወገን የሚተው አይደለም።
ድርጊቱ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ የተቃጣ አደጋ በመሆኑ ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
"አሁን የተጀመረው ትግል ከአንድ አሸባሪ ቡድን ጋር ብቻ አይደለም" ያሉት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የኮሚቴው ፀሐፊ አቶ ተፈሪ አባተ ናቸው።
ትግሉ ኢትዮጵያን የማዳን ተልዕኮ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ ፍቅርና ቁጭት ተነሳስቶ ሊሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በግንባር ለተሰለፈው የመከላከያና የጸጥታ አካለት ህብረተሰቡን በማስተባበር ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የኮሚቴው አባላት ለሥራው በቀረበው መነሻ ዕቅድ ላይ በመወያየት እና ዕቅዱን በማዳበር መግባባት ላይ መድረሱም ተመልክቷል።
በቀጣይ ጊዜ ሳይወስድ በተቀመጠው የጊዜ ስሌዳ መሠረት ዕቀዱን ወደተግባር ለመቀየር የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡