የተጣለባቸው ኃላፊነት በታላቅ ሀገራዊ ወኔና ቁርጠኝነት እንደሚወጡ የድሬዳዋ ፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የተጣለባቸው ኃላፊነት በታላቅ ሀገራዊ ወኔና ቁርጠኝነት እንደሚወጡ የድሬዳዋ ፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት አስታወቁ
ድሬዳዋ፤ሐምሌ 10 /2013 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ለህግ ለማቅረብ በሚካሄደው ዘመቻ በመሳተፍ የተጣለባቸው ኃላፊነት በታላቅ ሀገራዊ ወኔና ቁርጠኝነት እንደሚወጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት አስታወቁ፡፡
ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ለሚሳተፈው የድሬዳዋ አስተዳደር የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ትናንት ምሽት አሸኛኘት ተደረጎላቸዋል።
ከአባላቱ መካከል ዋና ሳጅን ኩማ ጀማል ለኢዜአ እንደተናገሩት፤በሀገራዊው የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ተልዕኮ መሳተፍ ልዩና የሚያኮራ ነው፡፡
ሀገርን ለማፍረስ ሌት ተቀን አፍራሽ ድርጊቱን እየፈጸመ ያለው የህወሃት አሸባሪ ቡድን የዜጎች ሁሉ ጠላት መሆኑን ገልጸው፤
የጥፋት ቡድኑን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ የተሰማራው የድሬዳዋ ቡድን የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ይወጣል።
ለሀገር ሰላምና ለዜጎች ደህንነት ጠንቅ የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለህግ በማቅረብ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት በማረጋገጥ ዘመቻ ላይ በመሳተፌ ታላቅ ደስታና ኩራት ይሰማኛል ያሉት ደግሞ ምክትል ሳጅን ኤፍሬም አብራሃም ናቸው፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝብ የሰጧቸውን ታሪካዊ ኃላፊነትና ተልዕኮ በታላቅ ገድል በመወጣት ሀገርን ለማሻገር በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
ምክትል ሳጅን ዮሐንስ ናደው በበኩላቸው፤ የሀገር ጥሪን በመቀበል የዘመቻ አካል በመሆናቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸው፤ለዚህ ታሪካዊ ተልዕኮ መስዋዕት መሆን ደግሞ የበለጠ እንደሚያኮራ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ አገርን የማዳን ዘመቻው በፍጥነትና በስኬት እንዲጠናቀቅ ለሠራዊት እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በወቅቱ እንዳሉት፤ ፖሊስ የሀገርንና የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ይከፍላል፡፡
ጁንታው ሀገርን ለመበታተንና ሰላሟን ለማናጋት ከጠላቶች ጋር ተቀናጅቶ የሚያከናውነው የሽብር ሴራና ተግባር በተባበረ ክንድ መፍትሄ እንደሚሰጠውም ተናግረዋል፡፡
ወደ ግዳጅ ቀጠና ያመራው ልዩ ኃይልም ይህን ተልዕኮ ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ እንዲያሳካ ነው ብለዋል፡፡
የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ በበኩላቸው፤ አሸባሪውን የህውሃት ቡድን ለህግ ለማቅረብ ለሚከናወነው ዘመቻ አስተዳደሩና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል።
የአሁኑም ትውልድ አንድነቱን በማጽናት ሀገር ላይ የተደቀነውን ሴራ ማክሸፍ ላይ መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ለልዩ ኃይሉ፣ ለመላው መከላከያ ሠራዊትና ለክልሎች ልዩ ኃይል ስኬታማ ሀገራዊ ዘመቻና ተልዕኮ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል፡፡
ህግ ለማስከበር በሀገራዊ ጥሪ ላይ ለመሳተፍ ሁሉም ፍላጎት ቢኖረውም የተቀረው የፖሊስ አባላትና ልዩ ኃይል የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ለዘመቻው መሳካት አበርክቶቱን ያጠናክራል ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሣ ጣሃ ናቸው።
በልዩ ኃይሉ አሸኛኘት ስነ-ስርዓት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ፣ የካቢኔ አባላት፣የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞች፣ አባገዳዎችና የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በተጠራው ሀገራዊ ጥሪ የድሬዳዋን ጨምሮ የክልሎች ልዩ ኃይሎች ወደ ግንባር በመሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡