ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በጥናትና ምርምር ብሎም ብሔራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በጥናትና ምርምር ብሎም ብሔራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ
ሀምሌ 10/2013 (ኢዜአ) በውጪ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል ጥሪ አቀረቡ።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሰላም ሚንስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለ“Defend Ethiopia” የዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በተካሄደው የበየነ መረብ ውይይት የሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት ሀገሪቱ ያጋጠማት ወቅታዊ ችግር ወደ ዲሞክራሲ የሚደረጉ ሽግግሮች ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ ነው ፡፡
ወደ ህግ ማስከበር እርምጃ ከመገባቱ በፊት በርካታ የሰላም እድሎች ተፈጥረውለት ሊቀበል ያልቻለው የህወሃት ሽብርተኛ ቡድን በተመሳሳይ መንግስት ለሰብአዊ ድጋፍ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሰው፣ ቡድኑ ተኩስ አቁሙን በመጻረር ህጻናትን ሳይቀር ወደጦር ማሰለፍ መቀጠሉ ሊወገዝ ይገባዋል ብለዋል ፡፡
በሀገራችን የተጀመረው የዘላቂ ሰላም ግንባታ የተፈጠሩ ችግሮችን ሳንፈታ ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ተገደን ወደህግ ማስከበር የገባንበት ሂደት ወደ ዲሞክራሲ ለምናደርገው ሽግግር እንደ አንድ ተግዳሮት የሚታይ በመሆኑ ለመፍታት የመላው ህዝብ ጥረትን ይጠይቃል ነው ያሉት ፡፡
ለውጡ ፈጣን በመሆኑ በሽግግር ላይ ያሉ ተመሳሳይ ሀገሮች ይህንን መሰል ተግዳሮት ያጋጠማቸው መሆኑን ያስታወሱት ወ/ሮ ሙፈሪያት ችግሩን በመፍታት ወደተሻለ የዲሞክራሲ ስርአት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል ፡፡
አክለውም የውጪ ጣልቃ ገብነትና የሚዲያዎች አሉታዊ ሚናም በሽግግር ሂደት እክል ሊፈጥሩ የሚችሉና በአንዳንድ ሀገሮችም የተፈጠሩ ለውጦች ረጅም ሂደት የጠየቁ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በውጪ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለሚደረገው ጥረት በጥናትና ምርምር እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ በመሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
በትግራይ ክልል ሰላም ከማስፈን አንጻር በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይትና መግባባት የተደረሰበት ተግባራዊ ስራዎች ተጀምረው እንደነበር አስታውሰዋል።
የሽብርተኛው ቡድን እነዚህን ወገኖች የተለያየ ስያሜ በመስጠት ለማሸማቀቅ የተደረጉ ዘመቻዎችንም አስታውሰዋል ፡፡
“Defend Ethiopia” ዩናይትድ ኪንግደም አመራሮች በበኩላቸው ለሀገራቸው ሰላምና መረጋጋት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ከመዋጋት በተጨማሪ ለሚገኙበት ሀገር የፓርላማ አባላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ዳያስፖራውን በማስተባበር ሀገሩ ለምታቀርብለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ እንደሰጡ ተናግረዋል።
በቀጣይነት ሊሰሩ ያቀዷቸውን ተግባራትም በዝርዝር ማቅረባቸው ተጠቅሷል ፡፡
አያይዘውም ወቅታዊ መረጃን በጊዜውና በአግባቡ ለዳያስፖራው አለመድረስ ዳያስፖራው የተሳሳተ መረጃን እንዲይዝ ክፍተት እየፈጠረ በመሆኑ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል ፡፡