ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በተለይ በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል- ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በተለይ በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር ገለጸ።

ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ለግንባታና የተለያዩ ቁሳቁሶች ወጪ የተደረገበት በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ግቢ ውስጥ የተገነባው የልጆች የሳይንስ ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሚቱ ኡሞድ፤ በሳይንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በተለይ በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ብለዋል።

የህፃናት ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፍላጎትን የማሳደግ ኃላፊነትም የመደበኛው የትምህርት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት።

በዘርፉ በተለይም የሳይንስ ማዕከላት ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የልጆች የሳይንስ ማዕከል ማቋቋሙ መልካም ጅማሮ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልፀዋል።

በህፃናት ላይ ሁለንተናዊ ስብዕና እና የአእምሮ ዕድገት ለውጥ ለማምጣት ህፃናትን ያማከለ በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይም የትምህርት ምርምር ተቋማት፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም የልጆች የሳይንስ ማዕከል መከፈቱ ልጆች በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ጠንካራ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል። 

ማዕከሉም እየተዝናኑ እና እየተጫወቱ ዕውቀትን የሚቀስሙበት በመሆኑ ለቀጣይ ሕይወታቸው ግብዓት ይሆናቸዋል ነው ያሉት።

በማዕከሉ የቀረቡት የሳይንስ ውጤቶች ከውጪ ብቻ መጥተው የቀረቡ ሳይሆኑ ሀገር በቀል ሳይንቲስቶች ጭምር የሰሯቸው ስለሆኑ ወደ ፊት እየተሻሻለ እንደሚሄድ ገልፀዋል።

የማዕከሉ ግንባታ 3 ዓመት የፈጀ ሲሆን የጀርመን ባህል ማዕከል 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እና የጀርመኑ የሳይንስ ማዕከል ፌኖሜንታ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ወጪ ያደረገው 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በመንግሥት ከተሰጠው 40 ሚሊዮን ብር ላይ ተቀንሶ የተወሰደ ሲሆን ቀሪው ገንዘብ ለወጣቶች ሳይንስ ማዕከል ግንባታ የሚውል ነው።

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ከ10 ዓመት በፊት በ49 ሰዎች እንደተቋቋመ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም