የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ለህግ ማስከበር ሃገራዊ ጥሪ ለመሳተፍ ሽኝት ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ለህግ ማስከበር ሃገራዊ ጥሪ ለመሳተፍ ሽኝት ተደረገለት
ጋምቤላ ሐምሌ 9/2023 (ኢዜአ ) የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል የህወሃት የሽብር ቡድንን የጥፋት ተልኮ ለመመከት በሚደረገው ትግል ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማምሻውን ሽኝት ተደረገለት።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በአሸኛኘት መረሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የልዩ ሃይሉ አባላት የአሸባሪ የህወሐት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ዘመቻ ለመቀልበስ በላቀ ቁርጠኝነት ግዳጃቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አሸባሪው የህወሐት ቡደን ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመው ግፍና በደል ሳያንሰው የለመደውን የጥፋት ሴራውን አሁንም መቀጠሉንም ተናግረዋል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ለሃያ ዓመታት ሲጠበቀው በቆየው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የክህደት ወንጀል የፈጸመው አሸባሪው የጥፋት ኃይል ላይ በተወሰደው ህግ የማስከበር ዘመቻ አከርካሪው ተመቶ የነበረ መሆኑን አስታውሰዋል።
“መንግስት ለህዝቡ ሰላምና መረጋጋት በማሰብና በሰጠው የጥሞና ጊዜም የማሰቢያ ጊዜ አግኝቶ ወደ ሰላም ሊመጣ ይችላል በሚል መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም የጥፋት ኃይሉ ከችግር ፈጣሪነቱ አልተቆጠበም” ብለዋል።
ይባስ ብሎ ኢትዮጵያን አፈራርሳለሁ እያለ የጦርነት ነጋሪቱን በመጎሰም በአማራ ክልል አዋሳኝ የተለያዩ ግንባሮች ውጊያ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ አሸባሪ ኃይል ሀገር ለማፈረስ የጀመረውን ዘመቻ ለመቀልበስ የክልሉ ልዩ ኃይል ከሌሎች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ጋር በመሆን ግዳጁን በላቀ ቁርጠኝነት እንዲፈጽሙ አሳሰበዋል።
ከልዩ ኃይል አበላቱ መካከል ረዳት ኢንስፔክተር አየለ አሸናፊና ሻለቃ ኡቶሊ ኦኬሎ በሰጡት አስተያየት አሸባሪው የጁንታ ቡድን እየሞከረ ያለውን ሀገር የማፍረስ እኩይ ተግባር በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት ለመቀልበስ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ሽኝት የተደረገለት የክልሉ ልዩ ሃይል በነገው ዕለት ወደ ግዳጅ ቀጣና ስምሪቱ እንደሚንቀሳቀሱ በመረሃ ግብሩ ላይ ተግልጿል።