የህዳሴው ግድብ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ተፈላጊነቷ ይጨምራል--የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ተፈላጊነቷ ይጨምራል--የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ድሬዳዋ ሐምሌ 9/2013 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ተጠናቆ ግድቡ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ከፍታ የሚመልስና በዓለም አደባባይ ተፈላጊነቷን እንደሚጨምር የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ፡፡
"የኢትዮጵያ የህዳሴ ዘመን ዕውን እንዳይሆን የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን ለመመከት በአንድነት መቆም ይገባናል" ሲሉም ምሁራኑ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት እየተከናወነ ያለው የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌት ተጠናቆ ግድቡ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ከፍታ ከመመለስ ባለፈ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተቀባይነት ያሳድገዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር አሰፋ ካሳ የግድቡ ግንባታና ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት የግብፅና የሱዳን እንዲሁም የዓረብ ሊግን ሴራ በዓለም አደባባዮች ለማጋለጥ አስችሏል፡፡
"ይህም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ጥረትና እውነት በማሳየት ጎልታ እንድትወጣ ያደርጋታል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያነገበችውን የፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ፣ ከጨለማና ከድሃነት የመውጣት ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ በራስ ሃብት የመጠቀም መብት ለዓለም፣ ለናይል ተፋሰስ ሀገሮችና ለአፍሪካ ህብረት ማሳወቋን እንድታጠናክር ጠይቀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምህር ዓቢይ ደምሴ በበኩላቸው "የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሀ ሙሌትና ዘንድሮ በውሱን ተርባይኖች የሚመነጠው ሃይል ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ከፍታ ለመመለስ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገሮች ያላት ክብርና ተፈላጊነት እንደሚጨምርላት ገልጸዋል፡፡
''ግድቡ ዕውን ሆኖ ከለማንና ካደግን በፖለቲካው፣ በምጣኔ ሃብትና በወታደራዊ ዘርፎች የመደራደር አቅማችን ይጨምራል'' ብለዋል መምህር ዓቢይ፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀምና የመልማት መብቷን የትኛውም ዓለም አቀፍ ህግ እንደማያግዳት ተናግረው በቅርቡ ግብፅና ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ያቀረቡባትን ክስ በአሸናፊነት መወጣቷ ሁነኛ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
"አሁንም በተገኘው ድል ሳንኩራራ ብቃትና ጥንካሬ ያላቸውን ዲፕሎማቶች በተገቢው ቦታ በፍጥነት በመመደብ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ማሳደግ ይገባል" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ማጠናከሯ ከውስጥና ከውጭ ጫና ለመፍጠር የሚደረግባትን ሴራ ትርጉም ባለው መንገድ ለማክሸፍና እውነታን ለዓለም ለማሳወቅ እንደሚያስችላት ምሁሩ አመልክተዋል፡፡
ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የማንነትና የአንድነት መገለጫ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የፎክሎርና የሥነ-ጽሁፍ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ነጋ አበራ ናቸው፡፡
"ልዩነትን ወደጎን ባደረገው፣ ብሔራዊ መግባባት በፈጠረውና በራስ መተማመንን በፅኑ መሠረት ላይ ባስቀመጠው ግድብ በተፈጥሮ ሃብታች የመልማት ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብታችንን የሚያንበረክክ ኃይል እንደሌለ ማሳየታችንን መቀጠል አለብን" ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለምና አፍሪካ ተቀባይነቷንና ከፍታዋን የሚያበስረው ግድብ እውን እንዲሆን በውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።