ቀጥታ፡

የህወኃት ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በመዳረጉ በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቀው መሆኑን የህግና ዲፕሎማሲ ምሁራን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 9/2013 ( ኢዜአ) የህወኃት ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በመዳረጉ በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቀው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግና ዲፕሎማሲ ምሁራን ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሃት ህፃናትን መልምሎ ወደ ጦርነት በማስገባት ወንጀል እየፈፀመ ይገኛል።

የህግ ምሁሩ ዶክተር ተስፋዬ አባተና የዲፕሎማሲ መምህር እንዳለ ንጉሴ ህወሃት እየፈፀመ ያለው ተግባር በአገሪቷም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ።

ቡድኑ እድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትን ለጦርነት መመልመሉና ማሰለፉ የጄኔቫ ኮንቬንሺንን የሚፃረር መሆኑን ምሁራኑ አንስተዋል።

የቡድኑ ደርጊት ህፃናትን በሚመለከት የተቀመጠውን ዲክላሬሺን ኦፍ ሚኒመም ስታንዳርድስ ሂውማኒታሪያን ራይትስና ሌሎች አለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚጥስ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሰብዓዊ መብትና ለህግ መከበር የሚሰራ ከሆነ ገለልተኛ ሆኖ በሃገር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከመሰረታቸው መገንዘብና አጥፊውን ማጋለጥ እንደሚገባም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ህግን ማስከበር ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እይታ ገለልተኛ አለመሆኑንም ምሁራኑ ይናገራሉ።

በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሃት የሚያደርጋቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለመኮነን ፈቃደኛ አለመሆኑ ለዚሁ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚጠበቅ አለመሆኑንም ዶክተር ተስፋዬ ተናግረዋል።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦች በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ላይ ተመስርተው አሸባሪ ቡድኑ የሚፈፅመውን ወንጀል የመሸፈንና መንግስትን የመወንጀል አዝማሚያ መስፋት እየታየባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መንግስት አርሶ አደሩ ወደ እርሻ ስራው እንዲሰማራና የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም የህወሃት ቡድን አጋጣሚውን ለተጨማሪ ጥፋት እያዋለው መሆኑን ምሁራኑ ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን እድሚያቸው ከ15 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን በመመልመል ወደ ጦርነት እያስገባ መሆኑ እየታወቀ በተለይም አለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ማየቱ አሳሳቢ መሆኑን ምሁራኑ ተናግረዋል።

በመሆኑም አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የሲቪክ ማህበራትና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ድርጊቱን በቅርበት ተከታትለው ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ሕፃናት በአእምሯቸው፣ በአካላቸውና ሥነ- ልቦናቸው ያልዳበሩ በመሆናቸው ለተለያዩ ችገሮች ተጋላጮች ስለሚሆኑ ጥበቃና ከለላ ያስፈልጋቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም