የህወሓትን ርዝራዥ ቡድንን ሴራ ለመቀልበስ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህወሓትን ርዝራዥ ቡድንን ሴራ ለመቀልበስ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 9/2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ ቡድን ሀገር ለማፍረስ የወጠነውን ሴራ ለመቀልበስ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡት ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት፤ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚጠበቅባቸውን ለመፈጸም ዝግጁ ናቸው።
በሀዋሳ የመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ወልዴ ድቻ አሸባሪው ቡድን ከጅምሩም የኢትዮጵያ አንድነትን በመሸርሸር ሀብት ሲበዘብዝና ዜጎችን ሲያሰቃይ መኖሩን አስታወሰዋል።
በዘር ከፋፍሎ የፈጸመው ግፍ ያስመረራቸው ዜጎች አሽቀንጥረው ቢጥሉትም፤ ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ በነበረው ምኞት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አሰቃቂ ድርጊት መፈጸሙንም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ያደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞ ህፃናትን በማሰለፍ ሀገርን ለማፍረስ መንቀሳቀሱን ገልጸዋል።
ይህንን የጁንታውን እኩይ ዓላማ ለመቀልበስም እንደ ዜጋ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ፊልጶስ ሳና በበኩላቸው፤ አሸባሪው ቡድን በተካነው የውሸት ፕሮፖጋንዳ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራትን በመጠቀም በሀገሪቱ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።
ዜጎች ቡድኑ በእጅ አዙር ሀገርን ለማፈራረስ የሚያደርገውን ሙከራ ማምከንና የሕግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚጥሩ ሃይሎች ጎን በመቀናጀት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ማስቆምና ወንጀለኞችን ማጋለጥ ለነገ የማይባል ድርጊት እንደሆነም አስተያየት ሰጪውገልጸዋል።
በተለይ በውስጥም ሆነ ውጭ ሃይሎች የተደቀነውን ሴራ በትብብር በመበጣጠስ የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ ግዴታችንን መወጣት አለብን ብለዋል።
የሀዋሳ ታቦር መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ኢያሱ ዮዶ ፤ የሀገሪቱን ሰላምና እድገት ያልተዋጠላቸው አሸባሪው ቡድንና ምዕራባያዊያን ያሴሩትን ደባ መግታትና ሕግ ማስከበር ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ሀገራዊ ለውጡ እንዳይጨናገፍ ሰላማችንና አንድነታችንን ማስጠበቅና መንግሥትን መደገፍ ይገባናል ሲሉምአስተያየት ሰጥተዋል።
ህጻናትን ለጦርነት እየመለመለ እስከማሰለፍ የደረሰው የሽብርተኛው ቡድን እኩይ ተግባር ሊኮነን እንደሚገባው አመልክተው፤ የትግራይ ህዝብም የቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ መሳሪያ መሆን እንደሌለበት ጠቁመዋል።
አባቶቻችን የኢትዮጵያዊያን ሉአላዊነት ላለማስደፈር በከፈሉት ዋጋ ቀና ብለን መሄድ ችለናል፤ ዛሬም ሀገራዊ አንድነታችንን ጠብቀንና ሉዓላዊነታችን በማስከበር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅብናል ብለዋል።