ቀጥታ፡

ጤና ሚኒስቴር በኮንትራት ቅጥር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ላይ ሲሰሩ የነበሩ 6 ሺህ 200 ባለሙያዎችን በቋሚነት ለመቅጠር ሂደት ላይ ነው

ሐምሌ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጤና ሚኒስቴር በኮንትራት ቅጥር በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ሲሰሩ የነበሩ 6 ሺህ 200 ባለሙያዎችን በቋሚነት ለመቅጠር ሂደት ላይ መሆኑን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር "ከራስ በላይ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ በአገሪቱ ለ4ኛ ጊዜ የሐኪሞች ቀንን አክብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ አለምጸሃይ ጳውሎስ ባስተላለፉት መልእክት የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ለሰጡት አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።

"የእናንተን የሙያ እገዛ ለሚሻው ወገናችሁ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ፣ ከራሳችሁ በላይ ሙያችሁን በማክበር ያለ እረፍት የሰጣችሁት አገልገሎት በምንም አይተካም" ብለዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽን፣ የተፈጥሮና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች ከህብረተሰቡ በፊት ራሳቸውን አሳልፈው መስጠታቸውን ተናግረዋል።

ከ60 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውሰው፤ "ለከፈሉት መስዋዕትነት ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል በኮንትራት ውል ተቀጥረው ሲሰሩ የቆዩ 6 ሺህ 200 ባለሙያዎች በቋሚነት  ለመቅጠር እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከአጋሮች ጋር በመተባበር ከሶስት ሺህ በላይ ሐኪሞችን በሚቀጥሉት ወራት ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው በበኩላቸው "ማህበሩ ከሚኒስቴሩ ጋር  በመሆን የሐኪሞችን መብት ለማስከበር እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

"ሐኪሞች ህብረተሰቡን ሲያገለግሉ እነሱም ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው" ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር አገር አቀፍ የጤና ባለሙዎችና እና ጤና ክብካቤ ሰራተኞች የምስጋና እና የእውቅና ሳምንት ከሐምሌ 11 እስከ 17 2013 ዓ.ም ለማከናወን በዝግጅት ላይ መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም