ቀጥታ፡

የአሸባሪ ቡድኑ ሀገርን ለማፍረስ የሚያደርገውን ትንኮሳ ለመመከት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጎባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ጎባ፤ ሐምሌ 9/2013(ኢዜአ) የህወሓት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የጀመረውን ትንኮሳ ለመመከት የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ በጎባ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመንግሥትን የተናጠል የተኩስ አቁም ባለመቀበል እየፈጸመ ያለው የሽብር ተግባር እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል።

መንግስት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር እየወሰደ የሚገኘውን የህልውና ዘመቻ እንደሚደግፉም ገልጸዋል፡፡

በጎባ ከተማ የቀበሌ  ሁለት ነዋሪ አቶ ሁሴን ሙሳ እንዳሉት፤  አሸባሪ ቡድኑ የመንግስትን የተናጠል   የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል አጎራባች ክልሎች ማጥቃቱ የአሸባሪነቱ ተግባር ማሳያ ነው፡፡


መንግስት የሀገሪቱን ሉኣላዊነት ለማስከበር ተገዶ የገባበት ህግን የማስከበር እርምጃ ትክክለኛ መሆኑን ስለምረዳ የሚጠበቅብኝን የዜግነት ድርሻ  ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡

ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገውን እኩይ ተግባር ለመቀልበስ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአንድነት በመንቀሳቀስ  ሊመክቱት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የከተማ ነዋሪ አቶ አለሙ ዳዲ ናቸው፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ተግባር ሳያንስ አሁን ደግሞ ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየፈጸመ የሚገኘው የጦር ወንጀል ይቅር የማይባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአሁኑ ዘመቻ የአንድ ክልል ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ላይ የመጣ ሉአላዊትን የማስከበር ታሪካዊ ኃላፊነት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ የቡድኑን ሀገር የማፍረስ እኩይ ዓላማ በአንድነት መመከት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

አቶ አበበ ታደሰ የተባሉ ነዋሪ  በበኩላቸው፤ ቡድኑ በህዝብና ሀገር ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን ጥቃት ለማክሸፍ ሁሉም ዜጋ በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣት በአንድነት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ እንዲመክቱት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

አስተያየት ሰጪው የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈለ ከሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የሚፈለግባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ሃገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በህብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ  እንደሌለ ያመለከቱት  አስተያየት ሰጪዎቹ ፤ የአሸባሪውን ቡድን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ በሚደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም