ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ባለፉት 11 ወራት ለሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ሰብዓዊ እርዳታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል-- የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9/2013 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ባለፉት 11 ወራት ለተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና ሰብዓዊ እርዳታ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያየ አይነት መንገድ ሀገራቸውን እየደገፉ ይገኛሉ።

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዳያስፖራው በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረገ ያለው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰለማዊት ዳዊት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዳያስፖራው ባለፉት 11 ወራት ለህዳሴ ግድብና ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከ220 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በተጨማሪም በተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፎች ላይም ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ለአብነት አንስተዋል።

የዲያስፖራው ማህበረሰብ በአጠቃላይ ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለአገሩና ህዝቡ የበኩሉን ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም ወቅታዊ አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ ረገድም ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በተጨማሪ ዳያስፖራው ባለፉት 11 ወራት ብቻ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ወደ ሀገር ቤት መላኩን ጠቁመዋል።

በተለያየ መንገድ ለሀገራቸውና ህዝባቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በአለም ላይ ባሉ አገሮች ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከዚህም ውስጥ  ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዲያስፖራዎች በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ አውስትራሊያ እና አፍሪካ  ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም