የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አርብ በሐዋሳ ልምምድ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አርብ በሐዋሳ ልምምድ ይጀምራል
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 32ኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አርብ በሐዋሳ ልምምድ ይጀምራል። በማጣሪያ ጨዋታው ኢትዮጵያ በምድብ አምስት ከኬንያ፣ ከሴራሊዮንና ከጋና ጋር ተመድባለች። ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ የማጣሪያ ጨዋታውን ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም በሐዋሳ ስታዲዮም ከሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ባለፈው ሳምንት ለማጣሪያው ጨዋታ 34 ተጫዋቾችን የመረጡ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ሪፖርት ማድረጋቸውን ፌዴሬሽኑ ለኢዜአ አስታውቋል። የቡድኑ አባላት ዛሬና ነገ የሕክምና ምርመራ የሚያደርጉ ሲሆን በውጭ አገራት ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በኋላ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ከሴራሊዮን አቻው ጋር ከመጫወቱ በፊት በተያዘው ወር በአስመራ ከተማ ከኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ የፌዴሬሽኑ መግለጫ ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያካሄደው ሰኔ 2009 ዓ.ም በባባ ያራ ስታዲየም ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ሲሆን አምስት ለዜሮ በሆነ ውጤት መሸነፉ የሚታወስ ነው። ጋና እና ሴራሊዮን በመጀመሪያ ጨዋታቸው ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የያዙ ሲሆን ኬንያ ሶስተኛ ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃን ይዛለች። በካሜሮን በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።