ቀጥታ፡

ህጻናትን ለጦርነት እየማገደ ያለውን አሸባሪው ህወሓት ሊወገዝ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

ሚዛን ፤ ሐምሌ 9/2013( ኢዜአ) ህጻናትን ለጦርነት በመማገድ በትግራይ ህዝብ ላይ ታሪካዊ ጠባሳ ለመጣል እየሰራ ያለው አሸባሪው ህወሓት ሊወገዝ እንደሚገባ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ተናገሩ።
በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ህግ መምህር ታደሰ አይበራ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ወደጎን በማለት የተሸነፈበትን ጦርነት በመቀጠል ሀገር እንዳትረጋጋ እያደረገ ይገኛል።

በተለይ ህጻናትን ለማያዋጣው ጦርነት በመመልመል አስታጥቆ ማሰለፉ ዓለም አቀፍ ህግን ከመተላለፍ ባለፈ በትግራይ ህዝብ ላይ ታሪካዊ ጠባሳ እንደሚጥል ገልጸዋል።

የዚህን አሸባሪ ቡድን ህገ ወጥ ድርጊት እንዲገታ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በይፋ ሊያወግዙት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የመንግስትን የተናጥል ተኩስ አቁም እርምጃ እንደሽንፈት በመቁጠር ህወሓት ዳግም እየፈጸመ ያለውን ወንጀል ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግበትም ጠይቀዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስት ንጹሀን ዜጎችን ከጥቃት ከመከላከል በተጨማሪ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት የዓለም መንግስታትን ከጎኑ ማቆም ቀዳሚ ሥራው ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

"ህወሓት የተሰጠውን የማሰላሰያ ጊዜ ሀገር ካልመራሁ በሚል ለጦርነት ማዋሉ ተስፋ መቁረጡን ያሳያል" ያሉት ደግሞ ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር ጌታሁን ተሾመ ናቸው።

"አሸባሪው የህወሓት ቡድን ቀድሞውንም ለህዝብ አሳቢ ቢሆን ኑሮ አርሶ አደሩ የመኸር እርሻውን በሚያከናውንበት ወቅት ዳግም ጦርነት አውጆ ጥፋት አይፈጽምም ነበር" ሲሉ አክለዋል።

ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ በህግም በሞራልም የሚያስጠይቅ ተቀባይነት የሌላው ተግባር መሆኑንም መምህሩ አመልክተዋል። 

የእዚህን የጥፋት ቡድን እንቅስቃሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስቆም የሀገሩቱን ህልውና ለመታደግ ሁሉም ዜጋ በአንድነት የሚሰለፍበት ወቅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም