ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለሕዳሴው ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ተጠየቀ

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 8/2013 (ኢዜአ) -የሕዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ በሚከናወኑ ተግባራት የድሬዳዋ አስተዳደርና መላው ህብረተሰብ የጀመሩትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ በመጪው እሁድ ከሐረሪ ክልል ወደ ድሬዳዋ እንደሚገባና በሚኖረው ቆይታም ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር የዋንጫውን መምጣት አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የህዳሴ ግድብ በልዩነት ውስጥ አንድነትን ያፀና የኢትዮጵያዊያን ታላቅ የብሔራዊ ማንነት መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል።

የህወሓት አሸባሪ ቡድንና የውጭ ጠላቶች ለግድቡ መሰናክል በመፍጠር ሀገርን ለማፍረስ የሚያደርጉትን አፍራሽ ተግባር መቀልበስ እንዲቻል ዜጎች አንድነታቸውን እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል።

ግድቡን ከዳር ለማድረስና የሀገሪቱን የሕዳሴ ዘመን እውን ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት የድሬዳዋ አስተዳደርና መላው ህብረተሰብ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ለወራት ቆይታ ካደረገበት ሐረሪ ክልል በመጪው እሁድ ድሬዳዋ እንደሚገባም አቶ ከድር አስታውቀዋል።

ዋንጫውን ለመቀበልና የግድቡን የባለቤትነት መንፈስ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማጽናት የተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎችም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንም ጠቁመዋል።

"ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በተጀመረበት ዋዜማ የግድቡ ዋንጫ ድሬዳዋ መግባቱን ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ የሕዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፀሐፊ ተወካይ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ በበኩላቸው፤ የዋንጫው ወደ ድሬዳዋ መምጣት የህብረተሰቡን ተሣትፎና የባለቤትነት መንፈስ እንደሚያጠናከር ገልጸዋል፡፡

ዋንጫው በድሬዳዋ ለ5 ወራት  በሚኖረው ቆይታ ኪነ ጥበባዊ ኩነቶች፣ የአደባባይ የቦንድ ሽያጭ፣ ህዝባዊ የፓናል ውይይቶች፣ የድጋፍና ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል፡፡

አቶ ገበየሁ እንዳሉት፤ ዋንጫው በዘጠኙ የከተማ ቀበሌዎች፣ በአራት የገጠር ክላስተሮች እና በሌሎችም አካባቢዎች እየተዘዋወረ ቆይታ ይኖረዋል።

በዚህም ሁሉንም ህብረተሰብ በማስተባበር ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ በድሬዳዋ ህብረተሰቡ በቦንድ ግዥና ስጦታ ከ86 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም