መንግስት በአሻባሪው ህወሃት ላይ እርምጃ በመውሰድ ህግ የማስከበሩን ስራ እንዲያጠናከር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በአሻባሪው ህወሃት ላይ እርምጃ በመውሰድ ህግ የማስከበሩን ስራ እንዲያጠናከር ተጠየቀ
አሶሳ ፤ሐምሌ 08 / 2013 (ኢዜአ) መንግስት በአሻባሪው የህወሃት ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ህግ የማስከበሩን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጠል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳመለከቱት፤ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያካሄደው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ሀገርን ከጥፋት የታደገ ነው፡፡
የጥፋት ቡድኑ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም በፕሮፓጋንዳ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አሳቢር አኑር ፤ጁንታው የጥሞና ጊዜውን የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፋፋት እያዋለው በመሆኑ እንቅስቃሴውን መግታት ይገባል ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ " ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ " የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ኢትዮጵያውያን ማውገዝና ለመመከትም ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ መነሳት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የሽብርተኛው ህወሃት የሀሰት ፕሮፓጋንዳና አሁን በሀገሪቱ በተግባር እየታየ ያለው ለውጥ ፈጽሞ እንደማይገናኙ የተናገሩት ደግሞ አቶ አጠይብ መሐመድ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው፡፡
ቡድኑ እንደከዚህ ቀደሙ ህዝብን ከህዝብ አጋጭቶ ወደ ስልጣን የሚመጣበት መንገድ መዘጋቱንም አስረድተዋል፡፡
''የሽብር ቡድኑ አቅም አልባ ሆኗል'' ያሉት አቶ አጠይብ፤ ብቸኛ ተስፋው የግብፅና የምዕራባውያን ሀገራት ድጋፍ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ጁንታው በተሰጠው የጥሞና ጊዜ መሰረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው መውጣትን ተጠቅሞ በትምህርት ገበታ መገኘት ያለባቸውን ህጻናት በጦርነት ለመማገድ መነሳቱ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አንድ ሰብዓዊ ፍጡር ድርጊቱን አወግዛለሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ ጎዳና እየመጣች መሆኑን በመረዳት የትግራይ ህዝብ ከወንድሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የህወሃት ጥረት ከፕሮፓጋንዳ አልፎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ የፌደራል መንግሥት እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ጠይቀዋል፡፡
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት ፤ አሸባሪው ቡድን ከፌደራል መንግሥት ጋር የፖለቲካ ተቃርኖ ብቻ ሳይሆን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በወሰደው ጥቃት ወንጀል መፈጸሙን አስታውሰዋል፡፡
በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውን ተግባር የፈጸመው አሸባሪ ቡድን መንግሥት ተኩስ በማቆም የወሰደው እርምጃ ለዳግም ጥፋት ማዋሉ እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት የሰጠው የጥሞና ጊዜ ተገቢ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መውጣትም አግባብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
''የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም'' ያሉት ምሁሩ፣ ህወሃት በማይችለው ጦርነት ገብቶ ከደደቀ በኋላ አሁን የሚያሰማው ፕሮፓጋንዳ እንደማያስገርም ገልጸዋል፡፡
በሽብርተኝት የተፈረጀ ተስፋ የሌለው አካል የመጨረሻ ግቡ ደግሞ አጥፍቶ መጥፋት ብቻ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጉዳይ ለዴሞክራሲ ዘብ ቆመናል የሚሉ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት ዴሞክራሲን የሚጻረር ተግባር ሲፈጽሙ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡
ሆኖም መንግሥት የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ሳይሰጥ የውጭ ኃይሎችን ጫና ለመቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡