የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ሴራ ለመመከት ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊቆም ይገባል- የምራእብ ወለጋ ዞን ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ሴራ ለመመከት ሁሉም ዜጋ በአንድነት ሊቆም ይገባል- የምራእብ ወለጋ ዞን ወጣቶች
ጊምቢ ሀምሌ 8/ 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገርና በሕዝብ ሰላምና ደህንነት ላይ የደቀነውን የጥፋት ሴራ ለመመከት ሁሉም ዜጋ በአንድነት ዘብ ሊቆም ይገባል ሲሉ በምራእብ ወለጋ ዞን ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ለ27 ዓመታት ሀገርን ሲዘርፍ የነበረው አሸባሪው ህወሓት አሁንም የሀገርን ሰላም በማድፍረስ እያደረሰ ያለውን ጥፋት ሁለም ዜጋ በአንድነት በመቆም ሊመክተው ይገባል ።
አሸባሪው ቡድን በመንግሥት የተላለፈውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ባለመቀበል የጥፋት ሴራውን እየቀጠለ በመሆኑ ለትንኮሳው የማያዳግም ምላሸ ለመስጠት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ወጣቶቹ ተናግረዋል።
ወጣቶቹ አክለው "አካባቢያችንን እያለማን ለሀገራችን ሰላም ዘብ እንቆማለን" ብለዋል።
በወጣቶች መስዋእትነት የተገኘውን ድል ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡም ወጣቶቹ ተናግረዋል።
የግምቢ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሳምሶን ሀብቴ በሰጠው አስተያየት "አሸባሪው ህወሓት ሃገሪቱን ሲዘርፍ፣ ወጣቶችን ሲገልና ለተለያዩ በደሎች ሲዳርጋቸው የቆየ ነው" ብሏል።
"አሸባሪው ቡድን አሁንም ሀገርን ካልዘረፍኩ እያለ እየተወራጨ በመሆኑ ከሃገር መከላከያ ጎን በመቆም የሀገሪቱን ሰላም ለማስከበር የበኩሌን ድርሻ እወጣለሁ" ብሏል፡፡
በገንጂ ወረዳ የቡሳኖ ቀዋሶ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል አስፋው በበኩሉ "የሀገራችንን አንድነት ለማፍረስ የሚንቀሳቀስ የትኛውንም ሀይል ለመመከት ያለኝን ጉልበትና ወጣትነቴን ለሃገሬ ሰላምና አንድነት ለማዋል ዝግጁ ነኝ" ብሏል፡፡
"ከመንግስት ጎን በመቆም ለሃገሬ ሰላምና አንድነት መከበር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ያለው ደግሞ ወጣት አዲሱ ዋቅቶላ ነው።
ከሀዲው ጁንታ በሀገር አንድነት ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት አንድ ሆኖ መመከት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ወጣቱ አመልክቷል።
የግምቢ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጫላ ታሲሳ በበኩላቸው "ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ቡድንና ርዝራዦች እንዲሁም አንዳንድ የውጭ ሀገራትና የውስጥ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ለማዳከም ሌት ከቀን ቢጥሩም አይሳካላቸውም" ብለዋል፡፡
"ኢትዮጵያ በህዝቦቿ እጥንትና ደም የተገነባች ሃገር በመሆኗ ማንም ሊያፈርሳት አይችልም" ሲሉ በአጽእኖት ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጅ ከሆነውና ከሀገር አልፎ በሌሎች ሀገራት ሰላም በማስከበር ዝናን ካተረፈው የሀገር መከላከያ ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ህልውና መታደግ የሁሉም ሃላፊነትና ግዴታ መሆኑን አቶ ጫላ አስገንዝበዋል።