ቀጥታ፡

አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን የማፈራረስ የጋራ ዓላማ ካላቸው ሃይሎች ጋር እየሰራ ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 8/2013 ( ኢዜአ) "አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን የማፈራረስ የጋራ ዓላማ ካላቸው ሃይሎች ጋር እየሰራ ነው" ሲሉ በዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።

የሰሙኑን የአሸባሪ ሕወሃት ትንኮሳ ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ በወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም አሸባሪው ሕወሃት ኢትዮጵያን በመራበት ዓመታት ሁሉ ኢትዮጵያኖች አንድ እንዳይሆኑ መስራቱን አስታውሰው፤ በኃይማኖት፣ በብሔርና በተለያየ አግባብ ሲከፋፍል መቆየቱን ሁሉም እንደሚያውቀው ገልጸዋል።

በተለይ ወጣቱ ባደረገው መራራ ትግልና በመንግስት ውስጥ ያሉ ለውጥ ፈላጊ ሀይሎች ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግል አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ማዕከላዊ የፖለቲካ ስልጣኑን ማጣቱን አስታውሰዋል።

ይህው የአሸባሪ ቡድን ከተጠያቂነት ለማምለጥ በመቀሌ ተሰባስቦ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ''እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ አትኖርም'' በማለት የአገር መከላከያ ሠራዊቱን መውጋቱንም አውስተዋል።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አሸባሪው የአገር መከላከያ ሠራዊትን በማጥቃት የአገር ሉዓላዊነትን በመዳፈር "አገርን የማፍረስ ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።

ይህ ድርጊቱ ኢትዮጵያን ለውጪ ጠላቶች ጥቃት ያመቻቸና ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን መጠቀም እንዳትችል ለጠላት አጋልጦ የሰጠ እንቅስቃሴ እንደሆነም ተናግረዋል።

''አሸባሪው እንዳሰበው አልሆነም እንጂ ሁኔታው ኢትዮጵያን ለውጪ ጠላት ወረራ አጋልጦ ለመስጠት ነበር'' በማለት ይገልጻሉ።

ዶክተር አለሙ እንደገለጹት፤ በአገር መከላከያ ሠራዊት ጀግንነት በደረሰበት ኪሳራ በየጉራንጉሩ ተደብቆ የቆየው ቡድን መንግስት ሰብዓዊነትን መሰረት ያደረገ የተናጥል የተኩስ አቁም ማዋጁን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ወረራ እያደረገ ይገኛል።

አጋጣሚ ሆኖ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ካለበት ቦታ ቀጥሎ ያለው መሬት የአማራ ክልል ወሰን መሆኑን ጠቁመው፤ ትንኮሳውም እዚያው በመጀመሩ ጉዳዩ የሁለቱ ክልሎች አድርጎ ማየቱ እጅግ የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን የሚሉ አካላትም በአሸባሪው ቡድን የተሰማሩ ካልሆኑ በስተቀር "ቡድኑ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያውቅ አካል ጉዳዩ የሉዓላዊነት መሆኑን አያጣውም" ነው ያሉት።

አሻባሪ የሕወሃት ቡድንም በግልጽ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ''ዓላማችን ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው ብለው ይናገራሉ" ያሉት ዶክተር አለሙ፤ አሁን ለማድረግ እየሞከሩ ያሉትም ይህንኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያን የማፍረስ፣ ለውጪ ጠላት አሳልፎ የመስጠት፣ የባንዳነት ስራ መሆኑን "ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊረዳው ይገባል" ብለዋል።

''አሸባሪው ቡድን የውስጥ ባንዳ ሆኖ ኢትዮጵያን ማፈራረስ ከሚፈልጉ የውጪ ሀይሎችና ቅጥረኞች ጋር እየሰራ ነው'' ይላሉ።

ቡድኑ በፈጸመው ትንኮሳ የተናጥል ተኩስ አቁሙ የከሸፈ መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የህልውና በመሆኑ የክልሎች የጸጥታ አካላት ጭምር እየተሳተፉበት አሻባሪው ልኩን እንዲያውቅ አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድበትም እንደሚገባ ተናግረዋል።

"አሁንም ያጋጠመን አገራዊ አደጋ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር በመንቀሳቀስ ልክ እንደከዚህ በፊቱ ድጋፋቸውን ሊያደርጉ ይገባል" ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስም ይሁን መንግስትን ከመጠራጠር ወጥተው "በአገር ላይ የመጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ሊረባረቡ ይገባል" በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

"ልክ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ እንዳጠናቀቅን ሁሉ ለአገራችን ክብርና ህልውና በጋራ መቆምና ትንኮሳውም የአሻባሪው ቡድን ብቻ አለመሆኑን መረዳት ይገባል'' ብለዋል።

ከሁሉም በላይ የውጪ ትላልቅ እጆች ከአሸባሪው ቡድን ጀርባ መኖሩን ጠቅሰው፤ ለዚህ ለጋራ አገር በጋራ የሚቆምበት ወቅት አሁን መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ካልሆነ አሁን ያጋጠመው ጉዳይ የኋላ ኋላ የታሪክ ተጠያቂነትን ጭምር እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ አሸባሪው ሕወሃት ህጻናትን ጭምር ወደ ጦርነት ሲማግድ እንኳን ዝም እንዳሉ አስታውሰው፤ በዚህም የቡድኑ አሰማሪዎች የኢትዮጵያ ጠላቶች መሆናቸውን መረዳት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ጫናና ተጽዕኖን ለመቋቋም በዋናነት አንድነትን ማጠናከርና በጋራ መቆም እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

ከዚህ ባለፈ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የመገናኘት እድሉ ያላቸው ዜጎች እውነተኛውንና ትክክለኛውን ገጽታ ማስረዳት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም