የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂን ይፋ አደረገ
ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።
ይፋ በማድረግ መርሃ-ግብሩ ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ እንዳሉት፤ ስትራቴጂው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ነው።
ስትራቴጂው በፋይናንስ ዘርፍ ያሉትን የዲጂታል ክፍተት በመለየት መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራትን ማካተቱንም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
ተጨባጭ፣ አካታችና ሊተገበር የሚችል መሠረተ ልማት መገንባት በዲጂታል ክፍያ ተወዳዳሪ ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ጠንካራ እና ወጥ የሆነ የቁጥጥር ማዕቀፍ መዘርጋትና ለፈጠራ ችሎታ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የስትራቴጂው ዋነኛ ማእቀፎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
“የተጠቀሱትን ማእቀፎች በመጠቀም የዲጂታል ክፍያ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል” ያሉት ምክትል ገዥው፤ የባንኮችን የክፍያ ሥርዓት እንደሚያቀላጥፍም አስረድተዋል።
የባንክ የክፍያ ሥርዓትና ሴትልመንት ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ስትራቴጂው ባንኩ የክፍያ ስርዓት ለማዘመን ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ስትራቴጂው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ክፍያን በአነስተኛ ወጪና ጊዜ አስተማማኝ በሆነ መልኩ እንዲፈጽም እንደሚያስችለው ተናግረዋል።
ባንኩ በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ላይ ለሚሰማሩ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ለባንኮች ብቻ ይፈቀድ የነበረው የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ፈቃድ ለአገር ውስጥ የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድ አውጪዎችና ለክፍያ ኦፕሬተሮች እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።
ስትራቴጂው ለሦስት ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።