ቀጥታ፡

በስምጥ ሸለቆና በምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 08/2013 (ኢዜአ) በስምጥ ሸለቆና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስጠነቀቀ፡፡

ዜጎች በየአካባቢያቸው ቆሻሻ የደፈናቸውን ቱቦዎች በማጽዳት እንዲሁም በመኖሪያ አካባቢ ብሎም በእርሻ ማሳ ዙሪያ የጎርፍ ማፋሰሻዎችን በማዘጋጀት ከወዲሁ የጥንቃቄ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 መጨረሻ ያሉት ወሮች የክረምት ወቅት ሲሆኑ፤በእነዚህ ጊዜያት ከደቡብና ከደቡብ ምሥራቅ ቆላማ አካባቢዎች በስተቀር በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ያገኛሉ።

የኤጀንሲው የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ ከመጋቢት አጋማሽና ሚያዚያ ወር ጀምሮ የደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ማግኘት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

ዝናቡ ወደ ሰሜንና መካከለኛው ምስራቅ እየተስፋፋ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ በተለይ በምዕራብ አጋማሽ የሚገኙ ከፍተኛ ቦታዎች በክረምት ወቅት ከፍተኛ የዝናብ መጠን እንደሚስተዋልባቸው ተናግረዋል፡፡

ከክረምቱ ጋር ተያይዞ መደበኛ፣ ከመደበኛ በላይ እና ወደ መደበኛ የተጠጋ የዝናብ መጠን በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስተዋልም ነው የገለጹት።

ኤጀንሲው የአየር ጸባይ ትንበያ መሰረት በስምጥ ሸለቆ አካባቢ፣ በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍልና ደቡብ አካባቢ ወደ ፎገራም  የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በወንዝ አካባቢ ወንዝ ከሚይዘው በላይ ዝናብ ዘንቦ ከሞላ  ጎርፍ የሚፈጠር ይሆናል። 

ከክረምት ወቅት ጋር ተያይዞ የዝናብ መጠን ስለሚጨምር የግብርና ባለሙያዎች ተስማሚ ዘር ለመምረጥ እንዲያግዛቸው የአየር ትንበያ መረጃን አስቀድመው ማግኘት እንዳለባቸውም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ሊከሰቱ የሚችሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ የአየር ትንበያ መረጃዎችን በመከታተል አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መክረዋል።

የክረምቱ የዝናብ መጠን ከሀገሪቱ ዓመታዊ የዝናብ ድርሻ ከ50 እስከ 85 በመቶ እንደሚሸፍን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም