በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል-የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8 ፤2013 (ኢዜአ)በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጪ ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 248 ሺህ 311 ቶን ቡና ወደ ውጭ መላኩን ገልጸው፤ በዚህም 907 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንፃር ሲታይ በመጠን 80 በመቶ በገቢ ደግሞ 77 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በታሪኳ ከቡና ምርት ከፍተኛ የተባለውን የውጭ ምንዛሪ ያገኘችበት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ገቢው በ2009 ዓ.ም ከተገኘው 882 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የ25 ሚሊየን ዶላር ብልጫ እንዳለውም ለአብነት አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ የመጨረሻ 5 ወራት ለዓለም ገበያ የቀረበው የቡና ምርት አፈፃፀም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ከመቶ እጅ በላይ እድገት ማስመዝገቡንም ተናግረዋል።
የአንድ ቶን ቡና ዋጋም ከ3 ሺህ 700 ዶላር ወደ 4 ሺህ ከፍ ያለ ሲሆን፤ ይህም ቡና በጥራት ለገበያ መቅረቡን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ለገቢው መጨመር የገበያ ትስስር ቀጥተኛ እንዲሆን እና በጥራት ላይ በከፍተኛ ትኩረት መሰራቱን በምክንያትነት አንስተዋል።