አሸባሪው ህወሃትን በማያዳግም ሁኔታ በመደምሰስ የሀገር ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል- የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃትን በማያዳግም ሁኔታ በመደምሰስ የሀገር ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል- የፖለቲካ ፓርቲዎች
ባህር ዳር፣ ሐምሌ 8/2013-(ኢዜአ) "ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን አሸባሪው ህወሓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ የህዝብና የሀገር ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ በአማራ ክልል የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስገነዘቡ።
አሸባሪውን ህወሓትን ለመደምሰስ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ሁሉ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።
ክልሎች የጸጥታ ሃይሎችን በመላክ የአሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ እያሳዩ ያለው ተነሳሽነት ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመች የማትፈርስ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑን ፓርቲዎቹ ለኢዜአ አስታውቀዋል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ህወሀት ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ አቋም ሲያራምድ የነበረ ድርጅት በመሆኑ የአማራ ግዛቶችን በወረራ በመያዝ ህዝቡን ለጭቆና ቀንበር ዳርጎት መቆየቱን አስታውሰዋል።
በተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ አላማጣና ኮረም፣ ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ነጻ ቢወጡም ሰሞኑን መልሶ ለመያዝ ጥረት ማድረጉን አውስተዋል።
የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የፈጸመው ዳግም ወረራ በአማራ ህዝብ ላይ ብቻ የማይቆም በመሆኑ ቡድኑን ለመደምሰስ መላ ኢትዮጵያዊያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአንድነት ተባብረው መቆም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"በድንበር ከትግራይ ክልል ጋር ስለሚጋራ በአንዳንዶች ዘንድ ጦርነቱን የአማራ ክልል ብቻ አድርጎ መሳል ተገቢነት የለውም" ያሉት አቶ ተስፋሁን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የመጣውን ሃይል መደምሰስ የሁሉም ሃላፊነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ለሰው ልጅ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ነጻነትና አብሮነት የቆመ ሁሉ ጸረ ህዝብና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን ሃይል ለማጥፋት በህልውና ዘመቻው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን ላይ ሌሎች ክልሎች የጸጥታ ሃይሎችን በመላክ አሸባሪ ቡድኑን ለመደምሰስ እያሳዩ ያለው ተነሳሽነት ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ ጸንታ የቆመች የማትፈርስና የማትነቃነቅ ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ መሆኑን አስታውቀዋል።
ህወሓት ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ደህንነት አሳልፎ መስጠቱን አቶ ተስፋሁን ገልጸው የውጭ ጫናን ለመቋቋም የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
"እውነትን መሰረት ያደረገ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመስራት የትህነግን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለዓለም ህዝብ በማጋለጥ የምዕራባዊያንን ጫና መቀነስ ይገባል" ብለዋል።
አሸባሪውን ድርጅት በተባበረ የህዝብ ክንድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
መንግስት የአሸባሪው ህውሃትን ርዝራዥ በማጽዳት የህዝብና የሀገር ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ድርጅታቸው በህልውና ዘመቻው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመሰለፍ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ የባህርዳርና አካበቢው ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታነህ ወርቁ በበኩላቸው ድርጅታቸው የአማራ ህዝብን መብትና እኩልነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"የአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጠላት የሆነው አሸባሪው ህውሃት ሰሞኑን ወደ ራያ፣ ማይጸብሪና ዋግ ኽምራ ዞን በመግባት ያደረሰው ጥቃት ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።
"ህውሃት በፈጸመው ዳግም ወረራ ህዝቡ ህይወቱን፣ አካሉንና ንብረቱን እያጣ ነው" ያሉት አቶ ጌታነህ"አሸባሪ ቡድን ማስወገድ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
ድርጅታቸው በህውሃት ሴራና ሸፍጥ የሀገርና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አብን ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በአሸባሪ ቡድኑ የተፈጸመን ወረራ ለመመከት አቋም መግለጫ በማውጣት አጋርነቱን ማሳየቱን አስታውቀዋል።
የፌደራል መንግስትና ሌሎች ክልሎች የኢትዮጵያ መሰረታዊ ጠላት የሆነውን አሸባሪው ህወሃትን ለማጥፋት በአንድነት በመሰለፍ የተጣለባቸውን ታሪካዊ ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
መላው የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶችና ህዝቡ መንግስት እያቀረበ ያለውን ጥሪ በመቀበል ህወሃትን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ተስፋ ለማለምለም በአንድነት እንዲሰለፉ መልዕክት አስተላልፈዋል።