የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ጥቃት አዋገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተከሰተውን ጥቃት አዋገዘ
አዲስ አበባ ነሃሴ 1/2010 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ዘርንና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገውን ጥቃት አዋገዘ። ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በክልሉ ከተሞች የተፈጠረውን ክስተት እንደሚያወግዝ አስታውቋል። አገራችን ኢትዮጵያ ታላላቅ እምቶችን ተቀብላ በፍቅር በማስተናገድ ከማንኛውም የአለም አገራት ቀዳሚ መሆኗ አለም የመሰከረላት ሃቅ መሆኑን ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠቅሷል። ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ የህዝቡን አብሮ የመኖር እሴት ድርጊትና የመላውን ሙስሊምና ክርስቲያን እምነት ተከታዮችን ልብ የሰበረ መሆኑንም ገልጿል። በጅግጅጋ አካባቢ የተካሄደው የቤተ እምነት ማቃጠል የእስልምና እምነት አስተምህሮ እንደማይወክልም ምክር ቤቱ አስታውቋል። በብጥብጡ የክርስትና እምነት ተከታዮች ቤተ እምነት ተቃጥለዋል፣ ዘርንና ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ክቡር የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ አካል መጉደሉና ንብረት መውደሙ ምክር ቤቱን እጅግ እንዳሳዘነ አስታውቋል። የእስልምና ሃይማኖት የሰው ልጅ ፍጡርን ክብር ባለው መንገድ መንከባከብ እንደሚገባ ቅዱስ ቁርዓን እንደሚያስተምር ያወሳው መግለጫው በጅግጅጋ እና አካባቢው የተፈጠረው አሳዛኝ ድርጊት ከእምነቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አትቷል። እስልምና የሌሎች እምነቶችን፣ ማምለኪያ ቦታዎችና መገለጫዎችን ማክበርና ከእምነቶቹ ተከታዮች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖርም ያስተምራል ሲል በመግለጫው ተጠቅሷል። ድርጊቱ አሁን በአገር ደረጃ የተጀመረውን የአንድነትና የፍቅር ጉዞ ህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን ተስፋ ለማደናቀፍ የታለመ በመሆኑ ህዝቡ ከመሰል ድርጊቶችና አመለካከት ራሱን እንዲያርቅ አሳስቧል።