ቀጥታ፡

ወጣቱ ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት የሃገር ህልውናን የማስጠበቅ አደራውን ሊወጣ ይገባል--የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች

ሰቆጣ፣ ሐምሌ 8/2013 (ኢዜአ ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን በግልፅ ያሳየ በመሆኑ ወጣቱ ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት የሃገር ህልውናን የማስጠበቅ አደራውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰላም የሽዋ አደግ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሳኔ ተከትሎ ለህዝቡ የጥሞና ጊዜ መስጠቱ መልካም እርምጃ ነው።

"ይሁን እንጂ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከመንግስት የተሰጠውን ውሳኔ ወደ ጎን በማለት የሽብር ስራውን በተለዋዋጭና  በስልታዊ ዘዴዎች አጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ እረፍት ማግኘትና በግብርና ስራ መሰማራት ሲገባው ቡድኑ ህፃናትን ጭምር በመጠቀም ዳግም ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ይባስ ብሎ የአማራ ክልል ወሰንን ጥሶ በመግባት የሽብር ስራውን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ድርጊቱ የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን ዳግም ያስመሰከረበት መሆኑን አመልክተዋል።

የሽብር ቡድኑ እንቅስቃሴ ዳግም እንዳያንሰራራ ለማድረግ መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊመክቱት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለይም ወጣቱ ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት የሃገር ህልውናን የማስጠበቅ አደራውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል ።

መንግስትም በአሸባሪው ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን የማያዳግም እርምጃ ኢትዮጰያውያንን በማስተባበር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ኢሳያስ ሞገስ በበኩሉ "ጁንታው እየፈፀመ ያለው እኩይ ተግባር በአንድ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን የሃገር ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ብሏል።

''መላ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመሆን የአሸባሪውን እኩይ ድርጊት መመከት ይገባናል" ብሏል።

''እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆምን የማናሸንፈው ሃይል እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው'' ያለው ወጣቱ ጁንታው የጀመረውን የሽብር ድርጊት ለመመከት ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በሃገሪቱ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች ጁንታው እየፈፀመ ያለው ድርጊት የሃገር ህልውና ላይ የተቃጣ መሆኑን በመገንዘብ ሃገሪቱን ሊጠብቁ እንደሚገባ ወጣት ኢሳያስ አሳስቧል።

አሁን ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር የህልውና ዘመቻም መደገፍ፣ ማገዝና መተባበር እንደሚገባ አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም