ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የቀጠናውን ስነ-ምህዳር በማረጋጋት የአየር ጠባይ ለውጥን ለመከላከል ፋይዳው የጎላ ነው- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8፤2013 (ኢዜአ)ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጠናውን ስነ-ምህዳር በማረጋጋት የአየር ጠባይ ለውጥን ለመከላከል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በጅማ ዩንቨርሲቲ የአካባቢ ደህንነት ጥበቃ ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ከሀገር አልፎ የቀጠናውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው።

የግድቡ መገንባት በቀጠናው አዲስ ሃይቅ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ ገልጸው፤ ይህም የአካባቢውን ስነ ምህዳር በበጎ ጎኑ ይቀይረዋል ብለዋል።

በሃይቁ ዳርቻዎች ከሚፈጠሩ አረንጓዴ አካባቢዎች በተጨማሪ ሃይቁን ከደለል ለመከላከል የሚሰሩ የተፈጥሮ ጥበቃ ተግባራት የቀጠናውን የአየር ጠባይ ለውጥ በመከላከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ግድቡ ይዞት የሚመጣውን ተጓዳኝ ጥቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ ረገድ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራም ነው የተናገሩት።

ይህን በማሳወቅ ረገድም ከዘርፉ ምሁራን ከፍተኛ ስራ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

የቀጠናው ሀገራት ግድቡ የአየር ጠባይ ለውጡን ለመከላከል ያለውን ፋይዳ ተገንዝበው በትብብር መስራት እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

"ግድቡ ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብጽና ሱዳንም ጭምር ነው" ያሉት ፕሮፌሰር አርጋው፤ የኢትዮጵያ ምሁራን ግድቡ ያለውን ጠቀሜታ በሚመለከት ከግብጽ አቻቸው ጋር ተቀራርበው ለመምከር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው፣ ግድቡ በቀጠናው በተለይም በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች የሚከሰት የጎርፍ መጥለቅለቅን ይከላከላል ብለዋል።

ይህም በቀጠናው የተረጋጋ ስነ ምህዳርና የኑሮ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ግብጽ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት መጠቀም የሚያስችላት የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት እንዳላት ጥናቶች እንደሚያሳዩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ምሁራን ይህን አጉልቶ በማሳየት ረገድ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ዶክተር ፋሪስ ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እየተከናወነ ሲሆን፤ የጸጥታው ምክር ቤት ግድቡን በሚመለከት የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲቀጥል ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም