ቀጥታ፡

በካናዳ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌትን በማስመልከት ሰላማዊ ሰልፍ ሊያካሄዱ ነው

ሃምሌ 8፤2013 (ኢዜአ) በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌትን በማስመልከት ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂዱ አስታወቁ።

ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበረው በካናዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥምረትና የኢትዮ-ካናዳ ኔትወርክ ለማህበራዊ ድጋፍ የተሰኘው ድርጅት ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጥምረት ሰብሳቢ ዶክተር ፍስሐ ሰለሞን፤ ሰልፉን ማዘጋጀት ያስፈለገው የሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ሙሌት አስመልክቶ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ያለውን ደስታ ለመግለጽ፣ ለግድቡ ግንባታ ያለውን ድጋፍና አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመር ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይሄም ለግድቡ ግንባታ ለሚያደርጉት ድጋፍ ተነሳሽነታቸውን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

"ግድቤ የኔ ነው"፣ "ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ መጠቀም መብቷ ነው"፣ "ኢትዮጵያ የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት የመጉዳት ፍላጎት የላትም"፣ "የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በመጀመሩ ደስ ብሎናል" እና ሌሎች ተጓዳኝ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ እንደሚተላለፉ አመልክተዋል።

በተጨማሪም "ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ" በሚል በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ውጫዊ ጫና የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሉም የካናዳ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አካባቢ ሰልፉን እንደሚካሄዱ ነው ዶክተር ፍስሐ ያስረዱት።

በካናዳ የተለያዩ የከተሞችና የግዛት ምክር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ አባላት በሰልፉ ላይ እንዲገኙ ጥሪ መደረጉን ጠቁመው፤ ተጽእኖ ፈጣሪ የሚባሉት ፖለቲከኞች ንግግር እንዲያደርጉ እቅድ መያዙን ገልጸዋል።

የካናዳ መገናኛ ብዙሃን ለሰልፉ ትዕይንት እንዲዘግቡ ጥሪ መደረጉን ገልጸው፤ ሰልፉ ካናዳ የኮቪድ-19 ወረሽኝን ለመከላካል ባወጣችው መመሪያን መሰረት አድርጎ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

"በሰላማዊ ሰልፉ የካናዳ መንግስትና ሕዝብ ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና በአባይ ወንዝ ላይ ያላት አቋም እንዲያውቁት እንፈልጋለን" ብለዋል ዶክተር ፍስሐ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚከናወነው ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት እንደሆነና የተፋሰስ አገራትን የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት አመልክተዋል።

በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለካናዳ መንግስት በአባይ ወንዝና በግድቡ ግንባታ ላይ ማብራሪያ በመስጠት "በጉዳዩ ላይ ግልጽ የሆነ መረዳት እንዲኖራቸው እየሰሩ ይገኛል" ብለዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በካናዳ የሚኖረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ 400 ሺ ዶላር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከድጋፉ በተጨማሪም ዳያስፖራው ለግድቡ የተዘጋጀውን ቦንድ በመግዛትና ለመግዛት ቃል በመግባት ለሕዳሴ ግድብ ያለውን አጋርነት እየገለጸ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ፍስሐ ያስረዱት።

ከሰላማዊ ሰልፉ በኋላ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሕዳሴ ግድቡን ግንባታና የአባይ ወንዝን አስመልክቶ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅስቀሳ የማድረግ ዘመቻ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በካናዳ የሚገኙ ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በተሟጋችነትና ባለው አቅም ሁሉ የሚያደርገውን ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ እድገትና ልማት ለሚቀርቡ ጥሪዎች ድጋፉን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንና ኢትዮጵያ የሚደርስባትን ውጫዊ ተጽእኖዎች በመመከት አገራዊ ሃላፊነቱን እንደሚወጣም አክለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በያዝነው ወር የተጀመረ ሲሆን፤ በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ሙሌቱ እንደሚጠናቀቅ በመንግስት በኩል ተገልጿል።

በሁለተኛ ዙር ሙሌት 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም