ቀጥታ፡

የህወሓት ርዝራዦችና ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሚያደርጉትን ፍትጊያ በቁጭት ለመቀልበስ ተነሳስተናል -አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 8/2013 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦችና ደጋፊዎች በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ሠላሟን ለማናጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስና ለመመከት ተነሳስተናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለተሰናዳው ለሲዳማ ክልል ልዩ ሀይል አባላት ትናንት ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ የሽኝት ስነ ስርአት ተካሂዷል።

በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ህወሓት ዜጎች በተባበረ ክንድ ከስልጣን ቢያስወግዱትም ተመልሶ ለመምጣት በሚያደርገው ጥረት ሀገሪቱን እየተፈታተናት ይገኛል።

"አሸባሪ ኃይሉ የመንግስትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በማያዳግም ሁኔታ ማስቆም ያስፈልጋል" ብለዋል።

"በተለይ ቡድኑ የኢትዮጵያን ከፍታ ከማይወዱና ሀብቷን በእጅ አዙር ከሚጠቀሙ ከጎረቤትና ኃያላን ሀገራት ጋር በመተባበር እያደረሰ ያለውን ፈተናና መዳፈር ሁሉም ዜጋ በቁጭትና በጋራ ለመቀልበስና ለመመከት ልንነሳሳ ይገባል" ብለዋል።

በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በጋራ በመመከት አንድነታችንን በማፅናት የህዝባችንን ክብር ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

"የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና ለማስከበር የሲዳማ ልዩ ሃይል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሰለፍ ቁርጠኛ አቋምና ወኔ በመሰነቅ ተነሳስቷል" ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ ለልዩ ሀይሉ ባስተላለፉት መልእክት "የጥንት አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል በፍጹም ጀግንነትና በልበ ሙሉነት በድል እንደምትመለሱ በመተማመን በክብር ሸኝተናችኋል" ብለዋል።

"የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከጎናቸው ይሆናል" ሲሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል ወቅቱ ለሚፈልገው ሀገራዊ ተልዕኮ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል።

በተለይ የሲዳማ ህዝብ ለ27 ዓመታት ሲጨቁነው ከነበረው ህወሓት አገዛዝ ተላቆ የራሱን ክልል በመሰረተበት ማግስት በሀገራችን ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት ልዩ ኃይሉ መነሳሳቱ የሀገር አለኝታነቱን እንደሚያስመሰክር ተናግረዋል።

"የጁንታው ቅጥረኛ የሆኑ አንዳንድ መገናኛ ብዙሀን አፍራሽ ሚና ሲጫወቱ እያየን እንገኛለን" ያሉት ኃላፊው "ቅጥረኞችን ለማሳፈርና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ልዩ ኃይሉ የበኩሉን ዋጋ እንደሚከፍል በግልጽ አሳይቷል" ሲሉም ተናግረዋል።

ለግዳጅ የተሰማራው ልዩ ኃይል አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ቦጋለ ገላልቻ ልዩ ኃይሉ ተልዕኮውን ለመወጣት ከነ ሙሉ ትጥቁ ዝግጁ መሆኑን በመግልጽ ግዳጁንም በዲሲፕሊን፣ በደስታና በሞራል ለመፈጸም ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

ከልዩ ኃይል አባላት መካከል ምክትል ሣጂን ማንአለብሽ ሁሴን ሀገራዊ ጥሪውን በደስታ መቀበሏን ገልጻ ግዳጇንም ጠላትን በማንበርከክ በጀግንነት ለመወጣት ጉጉት እንዳደረበት ተናግራለች።

የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እሷን ጨምሮ ሀገራዊ ጥሪውን በታላቅ ወኔና ደስታ ተቀብለው ለመዝመት ያላቸው መነሳሳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም