ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አረንጓዴ አሻራ ልማት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን ተገለጸ

ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 08/2013(ኢዜአ) በአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ስራ የገጠሩ ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።

በአስተዳደሩ ''ኢትዮጵያን እናልብሳት'' የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር እስካሁን አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞች መተከላቸው ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአስተዳደሩ የተተከሉት ችግኞች የጎርፍ ስጋት በመቀነስ ለግብርና ልማት በማዋል አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡

በተለይ የፍራፍሬ ችግኞች ለውጤት በመብቃታቸው አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን በቤተሰብ ደረጃ ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት እገዛ በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአስተዳደሩ ከተተከሉ የዛፍ ችግኞች መካከል 68 በመቶ በመጽደቅ ለውጥ እያመጡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ኢብራሂም ገለጻ፤ የችግኝ ተከላው በበጋ ወራት ከሚከናወኑት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር ትርጉም ያለው ለውጥ በገጠር ቀበሌዎች ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡

በተያዘው የክረምት ወቅት ሁለት ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል በሂደት ላይ ይገኛል።

ከእነዚህ የደን፣ የፍራፍሬና የጥላ ችግኞች መካከል ገሚሱ በውሃ ገብ ሥፍራዎች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተካሄደ ያለው የችግኝ ተከላ ዘላቂ ልማትና የገጠሩ ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ችግኝ መትከልና መንከባከብ የጎርፍ አደጋን በመቀነስ የድሬዳዋን ሞቃታማ አየር ለኑሮና ለሥራ ምቹ በማድረግ ወሳኝ ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ የሚተክላቸው ችግኞችን እንደ ልጆቹ ተንከባክቦ ለቁም ነገር ማብቃት ላይ እንዲረባረብ ምክትል ከንቲባው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘንድሮ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የምሥራቅ አፍሪካ ለማስተሳሰር በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ድሬዳዋ 200 ሺህ ችግኞችን ለጅቡቲ እንደምታቀርብ አስታውቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ የገንደ ሪጌ ገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶአደር ወይዘሮ ከድጃ አህመድ በሰጡት አስተያየት ''የዛሬ ሁለት ዓመት የተተከሉት ምርጥ የፓፓያ ዝርያዎች እያፈሩልኝ ነው፤ ከወራት በኋላ የተሻለ ገቢ አግኝቼባቼዋለሁ'' ብለዋል፡፡

ሌሎችም ፍራፍሬዎችን በጓሯቸው ማልማት ቢችሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከተሞክሯቸው በመነሳት ገልጸዋል።

አቶ ዘመድኩን ታፈሰ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፤ችግኞችን መንከባከብ ላይ የሚስተዋለውን ችግር መፍታትና ድሬዳዋን የተሻለች ውብ ከተማ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሆኖም በዋና ዋና ጎዳናዎች የተተከሉት ችግኖች በሰዎችና በእንስሳት እንዳይጠፉ ጥንቃቄ እንዲደረግም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም