የመከላከያ ሠራዊት 'ከራስ በላይ ለወገን' የሚለውን መርህ በተግባር እያስመሰከረ ነው - ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት 'ከራስ በላይ ለወገን' የሚለውን መርህ በተግባር እያስመሰከረ ነው - ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 08/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 'ከራስ በላይ ለወገን' የሚለውን መርህ መላበሱን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ እና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ ገለጹ።
ብርጋዴር ጄኔራል አለማየው ወልዴ በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ተፈናቅለው በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ ራች መጠለያ ቆይተው ወደ ዶቢ ቀበሌ መጠለያ ማዕከል የተመለሱ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ግዳጅ የተሰጣቸውን የአገር መከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን አነጋግረዋል።
እንደ ብርጋዴር ጄኔራል ገለፃ፤ ኮማንድ ፖስቱ ባከናወናቸው ተግባራት በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከቀዬያቸው የተፈናቅሉ ከ52 ሺህ በላይ ዜጎችን በመመለስ በተመረጡ ማዕከላት እንዲያርፉ ተደርጓል።
ኮማንድ ፖስቱ በየወረዳ መጠለያ ማዕከላት እንዲያርፉ የተደረጉ ዜጎችን ወደሚኖሩበት አካባቢ ሄደው አምራች የሚሆኑበትን መንገድ ለማመቻቸት የእርቀ ሰላምና ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከየቀዬያቸው ተፈናቅለው በተመረጡ ማዕከላት የሚገኙ ዜጎችን በአስተማማኝ ሁኔታ ጥበቃ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ ሠራዊቱ ''ከራስ በላይ ለወገን'' የሚለውን መርህ በተግባር እንዳስመሰከረ አረጋግጠዋል።
በቀጣይም በየአውደ ግዳጁ ያሉ የሠራዊት አባላት ጠላት የሚመጣበትን ቀዳዳ ሁሉ በመድፈን ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ቀድሞ የማክሸፍ ስራ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የሠራዊቱ አባላት በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፤ በየማዕከሉ ያሉ ወገኖችን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ጥበቃ እያደረጉ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።