በላይ ታደሰና ትግል ግዛው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውቱ ተመረጡ - ኢዜአ አማርኛ
በላይ ታደሰና ትግል ግዛው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እንዲያጫውቱ ተመረጡ
አዲስ አበባ ነሃሴ 1/2010 ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው የምሥራቅና የመካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር እንዲያጫውቱ ተመረጡ። የማጣሪያ ውድድሩ በታንዛንያ አዘጋጅነት ከነሐሴ 4 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል። ሁለቱ ዳኞች ኢትዮጵያን በመወከል በውድድሩ ላይ እንዲያጫውቱ መመረጣቸውን የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) በድረ ገጹ አስታውቋል። በውድድሩ ላይ በላይ ታደሰ የመሐል ዳኛ ሆኖ የሚያጫውት ሲሆን ትግል ግዛው ደግሞ በረዳት ዳኝነት የሚያጫውት ይሆናል። ዳኞቹ በአፍሪካ አህጉራዊና የክለብ ውድድሮች ላይ ረጅም ጊዜ የማጫወት ልምድ ያላቸው ሲሆን በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር /ፊፋ/ ኢንተርናሽናል የዳኝነት መታወቂያ ካላቸው 14 ወንድ ኢትዮጵያውያን መካከል ይገኙበታል። የሴካፋ ውድደር በ2011 ዓ.ም በታንዛንያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የሚሳተፍ አገር ለመለየት የሚካሄድ የማጣሪያ ጨዋታ ነው። የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እንድታስተናግድ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን /ካፍ/ የተመረጠችው ታንዛንያ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ /ሴካፋ/ የማጣሪያ ጨዋታን እንድታዘጋጅ በሴካፋ ተመርጣለች። የሴካፋ ጨዋታ በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄድ ይሆናል። በምድብ አንድ የተደለደሉት ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያና ሱዳን ሲሆኑ በምድብ ሁለት ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲና ዩጋንዳ ተደልድለዋል። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችን ይዞ ዛሬ ማለዳ ወደ ታንዛንያ አቅንቷል። ቡድኑ ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በታንዛንያ በሚካሄደው ጨዋታ ላይ የሚሳተፉ አገሮችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።