ቀጥታ፡

ሰራተኞቹ ለመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ጎንደር ሐምሌ7/2013 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ከ34 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ የሎጅስቲክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድጋፉን ያደረጉት በ35 የሴክተርና በ66 በክፍለ ከተማ ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞች ናቸው፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን በሀገር ደህንነትና በክልሉ ሕዝብ ላይ የደቀነውን ስጋት ለመመከት ሕዝባዊ ድጋፍ የሚያስተባብር አንድ አቢይና ሶስት ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ መገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከከተማው ነዋሪዎች ከአጎራባች የገጠር ቀበሌዎች 169 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ወደ ግንባር ለዘመተው ኃይል ድጋፍ ለማሰባሰብ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

እቅዱን ለማሳካትም ከመንግሥት ሠራተኞች፣ከከተማው ነዋሪዎች፣ ከባለሀብቶች፣ ከንግዱ ማህብረሰብ ፣በውጭ ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

የመንግስት ሰራተኞቹ የአንድ ወር ደመወዛቸውን መስጠታቸውን የገለጹት አቶ አደባባይ የከተማውን ማህብረሰብ በማወያየት ሀገርን ለማዳን ሕዝባዊ ደጀንነቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አቶ አደባባይ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም