ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት በ18 በመቶ ጨምሯል --የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ሀምሌ 7/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት በ18 በመቶ መጨሩን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት ማሻሸያ መርሃ-ግብር ነገ በይፋ የሚጀመር ሲሆን፤ የጤና እና ግብርና ሚኒስትሮች መርሃ ግብሩን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

መርሃ ግብሩም በዋናነት በአመጋገብ ስርዓት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ጤና የዜጎች አኗኗርን መፍጠር ላይ ትኩረት ያደርጋል ነው የተባለው።

በጤና ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ዶክተር ፍሬው ለማ በኢትዮጵያ ጤናማ የምግብ ስብጥሮችን የሚመገቡ ህጻናት ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ጤናማ የምግብ ስብጥሮችን የሚመገቡ ህጻናት ምጣኔ ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረበት አራት በመቶ ወደ 12 በመቶ ከፍ ማለቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ይህ ምጣኔ ከአጠቃላይ ህጻናት ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ይህም በህጻናት አካላዊና አዕምሯዊ እድገት እንዲሁም ጤናማ አኗኗር አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያመጣም ጠቁመዋል፡፡

በአመጋገብ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ከሀገሪቷ ዜጎች መካከል 33 በመቶ የሚሆኑት የደም-ግፊት በሽታ ተጠቂ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞትና የአካል ጉዳት በ18 በመቶ መጨሩንም ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴርን በመወከል መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው የመርሃ-ግበሩ ገቢራዊ መሆን ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ በሽታዎቸን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ አግኝተው በአእምሮና አካል የዳበሩ ሀገር ተረካቢዎች እንዲሆኑ እንደሚያግዝም አክለዋል።

መርሃ -ግበሩም የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የምግብ ስርዓት ማሻሸያ መርሃ-ግብር የማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ ግብር ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም