ቀጥታ፡

ለግድቡ ደህንነት መረጋገጥ ህዝብ የሰጠንን አደራ በብቃት እንወጣለን--የ22ኛው ክፍለ ጦር አመራሮችና አባላት

አሶሳ፣  ሐምሌ 06 / 2013 (ኢዜአ) ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ደህንነት እንድናረጋግጥ ህዝብ የሰጠንን አደራ ለመወጣት የተጠናከረ ጥበቃ እያደረግን ነው ሲሉ በመከላከያ ሠራዊት የ22ኛው ክፍለ ጦር አመራሮችና አባላት ገለጹ።

የህዳሴው ግድብ አካባቢ ደህንነት የሚያስከብሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባትን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በስፍራው ተገኝቶ አነጋግሯል፡፡

የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል አዘነ ሽመልስ እንዳሉት በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ አይኑ ብሌን የሚጠብቀው የህዳሴው ግድብ ያለምንም እንቅፋት እንዲጠናቀቅ ተገቢውን ጥበቃ እያደረገ ነው።

ሰራዊቱ በተለይም ለግድቡ ግንባታ የሚጓጓዙ ግብአቶች ያለ ስጋት ወደ አካባቢው እንዲደርሱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በጠረፍ አካባቢ ሊገባ የሚሞክር የትኛውንም ሃይል መጠበቅም ሌላው ሠራዊቱ ሀላፊነቱን እየተወጣበት ያለ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል ።

የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የምህንድስና ክፍልም በአካባቢው የሚካሄዱ የመንገድ ስራዎችን ቅየሳ በማከናወን ያደረገውን ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋጾ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

"የህዳሴ ግድብ ማለት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሠራዊቱ የደም ዋጋ ነው" ያሉት ኮሎኔል አዘነ ግድቡ የአንድነት መሠረት እንደሆነም ተናግረዋል።

እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀቶችን በአግባቡ ማጠናቀቅ የሀገርን ክብርና ከፍታ እንደሚጨምር አመልክተዋል።

ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት የጠቀሱት ኮሎኔል አዘነ "የህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ መሠል ተስፋ ሰጪ ፕሮጀክቶች እንዳይደናቀፉ የእኛ ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በህዳሴው ግድብ አካባቢ የሪፐብሊካን ጋርድ አባል የመቶ አለቃ ያዕቆብ አበጀ በበኩሉ የህዳሴው ግድብ የሀገር ህልውና ማሳያ በመሆኑ 24 ሰዓት ያለድካም ጥበቃ እያደረግን ነው ብለዋል ።

በሙያው ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገርም በግሉ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አካባቢ በመሥራቱ በእጅጉ ደስተኛ መሆኑን የገለጸው መቶ አለቃ ያዕቆብ ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት እየከፈለ ያለውን መስእዋትነት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክቷል።

"የውስጥና የውጭ ጠላቶች የህዳሴው ግድብን ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ሙከራ አይሳካም" ያለው ደግሞ የአስር አለቃ ጌራወርቅ ጥላዬ ነው።

"ሞራላችን ከአባቶቻችን የተረከብነው የአሸናፊነት ስሜት ነው" ያለው የሠራዊቱ አባል "የፕሮጀክቱ ሠራተኞችንና የግድቡን ደህንነት ማስጠበቅ ዋነኛ ትኩረታችን ነው" ሲል ተናግሯል።

"በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው አስከፊ ጥቃት በእጅጉ ያሳዘነንና ቁጭት የፈጠረብን ነው " ያለው ደግሞ የመቶ አለቃ ሰለሞን ጌታሁን ነው፡፡

"የተፈጠረብን ቁጭት የትኛውንም ግዳጅ በታላቅ ወኔ እንድንወጣ እያደረገን ነው" ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሠራዊቱ የሰጠውን ፍቅርና አክብሮት የጠቀሰው የመቶ አለቃ ሰለሞን ለግድቡ ግንባታ እየከፈለ ያለውን መስዋእትነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም