ቀጥታ፡

የከተሞችን የቆሻሻ አያያዝ በማዘመን ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል---ኢንጂነር አይሻ መሃመድ

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 7/2013 (ኢዜአ) የከተሞችን የቆሻሻ አያያዝ በማዘመን ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ "በዩ ኤን ሃቢታት" የተገነባው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፓይለት ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቋል።

በምረቃው ስነ ስርዓት ወቅት ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ በጃፓንና ስዊድን መንግስት ፈንድ የተገነባው የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ውጤታማና ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የሚሆን ነው።

መንግስት በቀጣይ አሥር ዓመታት የከተሞችን ጽዳትና ውበት ለመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

"በእዚህም በተለይ በርካታ ህዝብ በሚኖርባቸው ዋና ዋና ከተሞች የቆሻሻ አወጋገድን በማዘመን ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ሥራ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።

ተሞክሮው የጃፓን ሀገር የሆነው ይህ ፕሮጀክት ውጤታማና በተመጣጣኝ ወጪ  የሚከናወን ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ዘዴ መሆኑን ኢንጂነር አይሻ ተናገረዋል።

"ከባህር ዳሩ ፕሮጀክት ምርጥ ተሞክሮ በመገኘቱ ይህንን በማስፋት ከተሞችን ማራኪና ለኑሮ ተስማሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የ"ዩ ኤን ሃቢታት ኢትዮጵያ" የፕሮጀክቱ ማናጀር ዶክተር ብርሃኑ እስከዚያ በበኩላቸው፤ ለፕሮጀክቱ ግንባታ 745ሺህ የአሜሪካን ዶላር ወጪ መደረጉንና የሦስት ዓመት ጊዜ መፍጀቱን ተናግረዋል።   

ፕሮጀክቱ ለማህበረሰቡ ችግር ሲፈጥር የነበረውን ቆሻሻ በማስቀረት በተሻለ የአወጋገድ ዘዴ ማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የደረቅ ቆሻሻን የመበስበስ ሂደት በማፋጠንና ወደ አየር የሚለቀቀውን መርዛማ አየር በመቀነስ አካባቢን ጽዱና ለህብረተሰቡ ምቹ ለማድረግ የሚያስችል ውጤታማ ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።

"ፕሮጀክቱ በአነስተኛ ወጪ የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችልና ውጤታማ ነው'' ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካካ ናቸው።

ፕሮጀክቱ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ትግበራ እንደሆነና በጃፓን ሀገር ውጤታማ የቆሻሻ አያያዝ ስርዓት መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ በባህር ዳር ከተማ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ይህም አንዱ  የኢትዮጵያና ጃፓን መልካም ግንኙነት ማሳያ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳሃሉ በበኩላቸው፤ "ፕሮጀክቱ እስከ ቀጣይ ስድስት ዓመታት የባህር ዳርን ደረቅ ቆሻሻ ያለምንም ችግር ለማስወገድ የሚያስችል ነው" ብለዋል።

በ2 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ፓይለት ፕሮጀክቱ ደረቅ ቆሻሻ በፍጥነት እንዲበሰብስ የሚያደርግና ከቆሻሻው የሚወጡ በካይ ጋዞችን መቀነስ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።

የከተማዋን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ችግር ከመፍታት ባለፈ ለሌሎች አካባቢዎች ጥሩ ልምድ የተገኘበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ምረቃ ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር፣  የፌዴራል፣ ክልልና ከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም