ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሶስትዮሽ የሚኒስትሮች ጉባዔ ስምምነት ላይ በመድረስ ተጠናቀቀ

አዲ አበባ ግንቦት 8/2010 የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት በአዲስ አበባ ያካሄዱት 2ኛው የሶስትዮሽ ውይይት ከስምምነት ላይ በመድረስ በስኬት ተጠናቀቀ። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ሶስቱ አገሮች በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። ሶስቱ አገሮች ከደረሱባቸው ስምምነቶች መካከል የሶስትዮሽ መሰረተ ልማት ፈንድ ማቋቋም አንዱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን የሚያጠና ራሱን የቻለ ብሔራዊ ሳይንሳዊ የጥናት ቡድን እንዲመሰረት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በተጨማሪም ለጥናት አድራጊው ቡድን ጥያቄዎችንና ምልከታዎችን በሚያቀርቡበት ሁኔታ ላይ ተስማምተዋል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ የጀመሩትን ውይይት መቋጫ ለማበጀት አንድ እርምጃ መጓዛቸውን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ በሶስቱ አገሮች መሪዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ እልባት ያላገኙ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲቀርብ በመሪዎቹ አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል። በውይይቱ  የመሰረተ ልማት ፈንድ እንዲቋቋም በማድረግ ሦስቱ አገሮች በመንገድና በባቡር እንዲተሳሰሩና በንግድና ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አቅጣጫ መሪዎቹ አስቀምጠው ነበር። በባለሙያዎች ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት አንድ ሁለት እያለ 19ኛ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ የአሁኑ ስምምነት ወደ ዋና ውይይት ለመዝለቅ መንደርደሪያ እንደሚሆን ይታመናል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች እንዲያጠና የተመረጠው የፈረንሳይ አማካሪ ተቋምም እስካሁን በይፋ ያቀረበው የመነሻ ሪፖርት ብቻ ነው፡፡ አርቲላ እና ቢ አር ኤል የተባሉ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው የፈረንሳዩ አማካሪ ተቋም ያዘጋጀውን የመነሻ ሪፖርት ለሶስቱ አገሮች ካስረከበ የቆየ ቢሆንም ከሶስቱ አገሮች የሚሰጠውን ዝርዝር ግብረ መልስ ለመቀበል ገና እየተጠባበቀ ነው፡፡ ሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተሰባሰቡት የሶስቱ አገሮች የባለሙያዎች ኮሚቴ አባላት በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ለማቅረብ በቀጠሮ ተለያይተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም