ቀጥታ፡

የግድቡ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በአፍሪካ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው - ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ

ሐምሌ 07 ቀን 2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይበልጥ የአፍሪካ አገራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።

የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የአባይ ወንዝ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲቀየር የበኩሏን ሚና እየተወጣች ትገኛለች።

ግብጽና ሱዳን "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" የሚለውን አቋም በመጻረር የግድቡን ጉዳይ ወደማይመለከታቸው አካላት እየወሰዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ችግሩን የሚመለከታቸው አካላት ብቻ እንዲያዩት በማመን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው ጉዳይ ጽኑ አቋም ይዛ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የግድቡ የዲፕሎማሲ ስራ በአፍሪካዊ መፍትሄ ላይ መመስረት እንደሚገባው ጠቅሰው፤ የናይል ተፋሰስ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ነገ ሊደርስባቸው እንደሚችል ማስገንዘብ እንደሚጠበቅባት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ግድቡን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች አፍሪካ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ምሁራን እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ ግንባታ በሙያቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀው፤ “በቀጣይም ለበለጠ ኃላፊነት ሊዘጋጁ ይገባል” ብለዋል። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ በራስ አቅም ከድህነት የመውጣት ጥረት መሆኑን በማስገንዘብ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም