ቀጥታ፡

ግድቡን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይበልጥ አፍሪካ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው- ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ

አዲስ አበባ ሃምሌ 7/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የህዳሴ ግድብን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ይበልጥ የአፍሪካ አገራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የአባይ ውኃ ጉዳይ ተመራማሪው ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።

ዶክተር ያቆብ አርሳኖ ላለፉት 40 ዓመታት በአባይ ወንዝ ዙሪያ ምርምሮችን በማካሄድ፣ በማስተማር፣ መንግስትን በማማከር እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል በመሆን ሀገራቸውን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ከአንድ መቶ በላይ የምርምር ስራዎችንና ጆርናሎችንም አሳትመዋል።

ዶክተር ያቆብ አርሳኖ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በእውቀትና ክህሎት ላይ በተመሰረተ አግባብ ያላትን የውሃ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ትገኛለች።

በአባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየውን ኢ-ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲቀየርም የበኩሏን ሚና እየተወጣች መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" የሚል ጽኑ አቋም እንዳላት ጠቅሰው፤ ነገር ግን ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብን ጉዳይ ወደ ማይመለከታቸው ሀገራት ለመውሰድ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

የጸጥታው መክር ቤት ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት መመለሱም ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ አንጻር የናይል ተፋሰስና ከተፋሰሱ ውጭ ያሉ የአፍሪካ ሀገሮች በኢትዮጵያ ላይ የሚስተዋለው የዲፕሎማሲ ጫና ነገ በእነርሱ ላይ ሊደገም እንደሚችል ማስገንዘብ ይጠበቅባታል ነው ያሉት።

በመሆኑም ግድቡን በሚመለከት የሚከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች አፍሪካን መሰረት ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ዶክተር ያቆብ ተናግረዋል።

ምሁራን እስካሁን ባለው ሂደት ለግድቡ ግንባታ በሙያቸው ያበረከቱትን አስተዋጽኦ አድንቀው፤ በቀጣይም ለበለጠ ኃላፊነት ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሃብት በእውቀትና ክሎት እንዴት መጠቀም እንዳለባት ያመላከተ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህም በቀጣይ በዘርፉ ለሚከናወኑ ስራዎች ትልቅ ግብዓት መሆኑን አብራርተዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ በራስ አቅም ከድህነት የመውጣት ጥረት መሆኑን በማስገንዘብ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት የጽጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህ

ብረት ጥላ ስር እንዲከናወን መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም