ለትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ በቀጥታ በረራም ሆነ የሀገር ሉዓላዊነትን በሚጥስ ሌላ ተግባር የሚደረግ እንቅስቃሴ አይፈቀድም--ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ለትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ በቀጥታ በረራም ሆነ የሀገር ሉዓላዊነትን በሚጥስ ሌላ ተግባር የሚደረግ እንቅስቃሴ አይፈቀድም--ኮሚሽኑ
ሃምሌ 7/2013 (ኢዜአ) ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ በቀጥታ በረራም ሆነ የሀገር ሉዓላዊነትን በሚጥስ ሌላ ተግባር የሚደረግ እንቅስቃሴ የማይፈቀድ መሆኑን ኮሚሽኑ አስወታወቀ።
ሃምሌ 7/2013 (ኢዜአ) ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ በቀጥታ በረራም ሆነ የሀገር ሉዓላዊነትን በሚጥስ ሌላ ተግባር የሚደረግ እንቅስቃሴ የማይፈቀድ መሆኑን እና በዚህ ረገድ ዜጎች ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በአለም ምግብ ፕሮግራም በኩል እየተደረገ ባለው ድጋፍ በነገው እለት ምግብ አና ምግብ ነክ ያልሆኑ 47 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ እንደሚጓዙም ገልጿል።
የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ በዓለም ምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በኩል ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የእርዳታ አቅርቦቶች በተገቢው መንገድ ወደ መቀሌ እንዲያጓጓዙ መንግስት ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
በዚሁ መሰረት ነገ ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ሰመራ 47 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ የሚጓጓዝ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 22 ከባድ ተሽከርካሪዎች 7 ሺህ 649 ኩንታል የምግብ አቅርቦት የጫኑ ናቸው።
ቀሪ ተሽከርካሪዎች ደግሞ 7 ሺህ 300 ኩንታል የሚሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን እንደጫኑም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ሲወስን ለአርሶ አደሩ በሰጠው ትኩረት መሰረት ከአጋር ድርጅቶች የግብርና ሥራዎች ለማፋጠን 10 ሺህ 359 ኩንታል ምርጥ ዘር በ12 ከባድ ተሽከርካሪዎች ለማጓጓዝ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ለቀረበ ጥያቄ ፈቃድ መሰጠቱንም አመልክተዋል።
መንግስት የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚሰጡትን እርዳታ እንዳይስተጓጎልና በወቅቱ እንዲደርስ ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት በቀጥታ በረራ በማድረግና ከአውሮፕላን ላይ በመጣል እርዳታውን የማቅረብ ጥያቄ እንዳላቸው አብራርተዋል።
ሆኖም የቀጥታ በረራም ሆነ ከአውሮፕላን ላይ እርዳታ መጣል የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል።በተባበሩት መንግስታት ለሰብዓዊ ድጋፍ የአየር በረራ አገልግሎት እንዲፈቀድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሰው ኃይላቸውን ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ይዘው እንዲሄዱ መፈቀዱን አስታውሰው፤ በማንኛውም ሁኔታ "ልዩና የቀጥታ በረራ" የሚባል ፈቃድ እንደሌለ ተናግረዋል።
በአየር ትራንስፖርት እንዲጓጓዝ በማድረግ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ድርጊት እንደማይፈቀድም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።እስከ አሁን በክልሉ ከተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ውስጥ 70 በመቶ በመንግስት ሲሸፈን፤ 30 በመቶው ደግሞ በእርዳታ ሰጪ አጋሮች መሸፈኑ ይታወቃል።የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ 400ሺ ኩንታል የምግብ እህልና አልሚ ምግቦችን በመቀሌ በመጋዘን ማስቀመጡን የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መግለጹ ይታወሳል።
የግብርና ሚኒስቴርም የተናጠል ተኩስ አቁም እስኪያደርግ ድረስ ለመኸር እርሻ የሚሆን 617 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ማስገባቱን ማስታወቁም እንዲሁ።
የዓለም አቀፍ ተቋማት አገሪቷ ባስቀመጠችው አቅጣጫ መሰረት በተገቢው መንገድ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርሱ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውም ተገልጿል።