የኢትዮጵያን ደማቅ የኦሎምፒክ ታሪክ አጽንታችሁ ተመለሱ-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ደማቅ የኦሎምፒክ ታሪክ አጽንታችሁ ተመለሱ-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ሃምሌ 07/2013(ኢዜአ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ "የኢትዮጵያን ደማቅ የኦሎምፒክ ታሪክ አጽንታችሁ ተመለሱ" በማለት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ለሚወዳደሩት አትሌቶች ሽኝት አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የኢተዮጵያ የሉዑካን ቡድን አሸኛኘት አድርገዋል።
ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድርን በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ ለኢትዮጵያና አፍሪካ አንጸባራቂ ድል አስመዝግቧል ሲሉ አስታውሰዋል ፕሬዚዳንቷል።
የአበበ ቢቂላን ፈር በመከተል በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን፣ በአስር ሺ እና አምስት ሺ ሜትር በማሸነፍ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
አትሌት ኮሮኔል ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና ኦሎምፒክ ድል በመቀዳጀት የመጀመሪያዋ ሴት ጥቁር አፍሪካዊት በመሆን ለመላው ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት መሆን ችላለች ብለዋል።
የጀግኖች አትሌቶች አሸናፊነት መሰረት የኢትዮጵያዊነት የአሸናፊነት ወኔ መሆኑን ገልፀው፤"የኢትዮጵያን ደማቅ የኦሎምፒክ ታሪክ አጽንታችሁ ተመለሱ" በማለት አትሌቶቹን አበረታተዋል።
በዘንድሮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ይህንን አይበገሬነት በመላበስ የሀገራቸውን ስም እንዲያስጠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
"የኢትዮጵያን የኦሎምፒክ ደማቅ የወርቅ ታሪክ በደማቁ አጽንታችሁ ተመለሱ" ሲሉም ፕሬዚዳንቷ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 65 ዓመታት በኦሎምፒክ ስፖርት 54 ሜዳሊያዎች ማግኘቷንና ከእነዚህም ውስጥ 22ቱ ወርቅ መሆኑንም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አስታውሰዋል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ስፖርት የምትወዳደርባቸውን ዘርፎች በማብዛት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።
"የእናንተ ማሽነፍ የኢትዮጵያ ማሸነፍ ነው።" ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍም አትሌቶች በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ህዝብ የሰጣቸውን አደራና ኃላፊነት በመወጣት የኢትዮጵያን የኦሎምፒክ ደማቅ ታሪክ እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው በኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ከቀደምት የዘርፉ ባለድሎች የተረከቡትን የድል አድራጊነት ትውፊት እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች እንደ ቀደሙት ጀግኖች የራሳቸውን አዲስ ታሪክ በላባቸው እንዲጽፉም የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
"ብዙ ሆናችሁ እንደ አንድ ለጋራ ድል መሰለፍ አለባችሁ" ሲሉም ነው የገለጹት።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ አትሌቶቹ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በሽኝት ስነስርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ለኦሎምፒክ ሉዑክ ቡድኑ በክብር አስረክበዋል።
ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ ውሃ ዋና እና በብስክሌት ውድድሮች የምትሳተፍ ሲሆን በተለይ በአትሌቲክስ ዘርፍ ለድል ከሚጠበቁ ግንባር ቀደም ሀገሮች አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ አትሌቶች ከስምንት መቶ ሜትር እስከ ማራቶን ያሉ ርቀቶችን ጨምሮ በሶስት ሺህ መሰናክልና በእርምጃ ውድድር የሚሳተፉ ይሆናል።