ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ደቡብ ሱዳን አጋርነቷን አሳይታለች -በደቡብ ሱዳን የክብር ቆንስላ አይሸሽም ተካ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ለመፍታት ደቡብ ሱዳን አጋርነቷን አሳይታለች -በደቡብ ሱዳን የክብር ቆንስላ አይሸሽም ተካ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለመፍታት ደቡብ ሱዳን አጋርነቷን አሳይታለች ሲሉ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ አቶ አይሸሽም ተካ ተናገሩ።
የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ህዝቦች ትብብርና አብሮነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በደቡብ ሱዳን ቆይታቸው በሰላም፣ ልማት እና ሰብዓዊ ድጋፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እኤአ በ2019 ከደቡብ ሱዳን መንግስት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል አቶ አይሸሽም።
የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን ግንኙነትንና ሌሎች ወታደራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ትብብርና አብሮነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ድንበር ከመጋራት ባለፈ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተሳሰሩ የሁለት አገር አንድ ህዝቦች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት ደቡብ ሱዳን አጋርነቷን አሳይታለች ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱ ሀገሮች ካላቸው የጠበቀ ወዳጅነት አንጻር ደቡብ ሱዳናውያን ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ይቆጥሯታል ነው ያሉት አቶ አይሸሽም።
በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ በኢጋድ በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበራት አስረድተዋል።
አሁን ደግሞ ደቡብ ሱዳን በሁሉም መስክ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ዘላቂ አጋርነቷን ማሳየቷን አድንቀዋል።
የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯ ጎረቤት አገራትንም ማእከል አድርጋ መስራቷ ለጋራ የልማት ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ትብብርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገራል።
ሁለቱ አገሮች የወታደራዊ ደህንነቶች መረጃ ልውውጥ፣ ድንበር ላይ የሚደረጉ ህገ-ወጥ የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውርን በጋራ ለመግታት በየካቲት 2013 ዓ/ም ስምምነት ማድረጋቸውም ይታወሳል።